Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 “ሥጋ የለበሰ ሰው ዕድሜው አጭር ነው፤ ያውም ቢሆን በመከራ የተሞላ ነው።

2 እንደ አበባ ታይቶ ወዲያውኑ ይረግፋል፤ እንደ ጥላም ብዙ ሳይቈይ ወዲያው ያልፋል።

3 ታዲያ እንዲህ ዐይነቱን ሰብአዊ ፍጡር ትከታተላለህን? በፊትህስ ለፍርድ ታቀርበዋለህን?

4 ከርኩስ ነገር ንጹሕ ነገርን ማግኘት የሚችል ከቶ ማንም የለም።

5 የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው፤ የሚኖርባቸውም ወራት በአንተ ዘንድ የተቈጠሩ ናቸው፤ አንተም ከወሰንክለት የዕድሜ ገደብ የሚያልፍ የለም።

6 ቅጥረኛ የቀን ሥራውን ሲፈጽም እንደሚደሰት፥ ሰውም በድካም ዘመኑ እንዲደሰት ታገሠው።

7 “ለተቈረጠ የዛፍ ጒቶ እንኳ ተስፋ አለው፤ እንደ ገና ሊያቈጠቊጥና ቅርንጫፎችም ሊያበቅል ይችላል።

8 ምንም እንኳ ሥሮቹ በመሬት ውስጥ ቢያረጁ ግንዱም በዐፈር ውስጥ ቢበሰብስ፥

9 የውሃ ጠል ካገኘ እንደ ገና ያቈጠቊጣል፤ እንደ አዲስ ተክልም ቅርንጫፎችን ያወጣል።

10 ሰው ግን ሞቶ እንዳልነበረ ይሆናል፤ ከሞተ በኋላስ የት ይገኛል?

11 “የሐይቅ ውሃ ተኖ እንደሚያልቅ፥ የወንዝም ፈሳሽ እንደሚደርቅ፥

12 ሰውም እንዲሁ ከሞተ በኋላ አይመለስም፤ ሰማይ እስከሚያልፍ ድረስ አይነቃም፤ ከእንቅልፉም አይነሣም።

13 “ምነው፥ በሙታን ዓለም ብትሰውረኝ! ቊጣህም እስከሚያልፍ ብትሸሽገኝ! የቀጠሮም ቀን ወስነህ ብታስበኝ!

14 ሰው ከሞተ በኋላ በሕይወተ ሥጋ ሊኖር ይችላልን? ዕረፍቴ እስከምትመጣበት ጊዜ ድረስ፥ ይህን የትግል ዘመኔን ፍጻሜ በትዕግሥት እጠባበቃለሁ።

15 በዚያን ጊዜ አንተ ትጠራኛለህ፤ እኔም ‘አቤት’ እልሃለሁ፤ ፍጡርህ የሆንኩትን እኔን ለማየት ትናፍቃለህ።

16 እነሆ አሁን እርምጃዬን ሁሉ ትከታተላለህ፤ ሆኖም ኃጢአቴን አታስብብኝም።

17 በከረጢት ታሽጎ እንደሚወረወር ጒድፍ በደሌን ሁሉ ታስወግድልኛለህ ኃጢአቴንም ትደመስስልኛለህ።

18 በዚህ ዓለም ግን የተራራ ናዳ እንደሚፈልስ፥ ቋጥኝም ከቦታው እንደሚፈነቃቀል፥

19 ውሃ ድንጋይን እየቦረቦረ እንደሚጨርስ፥ ኀይለኛ ዝናብም መሬትን እንደሚሸረሽር፥ አንተም እንዲሁ የደካማን ሰው ተስፋ ታጠፋለህ።

20 ኀይልህ ለዘለዓለም በእርሱ ላይ ይበረታል፤ እርሱም እንዳልነበረ ይሆናል፤ መልኩንም ለውጠህ ከፊትህ ታስወግደዋለህ።

21 ልጆቹ ክብር ቢያገኙ አያውቅም፤ ቢዋረዱም አያይም።

22 እርሱ የገዛ ሰውነቱ ሥቃይ ይሰማዋል፤ ስለ ራሱም ችግር ብቻ ያለቅሳል።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告