Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 “እነሆ፥ ይህን ሁሉ ዐይኔ አይቶታል፤ ጆሮዬም ሰምቶ አስተውሎታል።

2 እናንተ የምታውቁትን ያኽል እኔም ዐውቃለሁ፤ ከቶ ከእናንተ የማንስ አይደለሁም።

3 ነገር ግን የእኔ ንግግር ከኀያሉ እግዚአብሔር ጋር ነው፤ ከእርሱ ጋርም እከራከራለሁ።

4 እናንተ ግን በሐሰት የተሞላችሁ ናችሁ፤ ማንንም መፈወስ እንደማይችሉ ሐኪሞች ናችሁ።

5 ይልቅስ ዝም ብትሉ ኖሮ ጠቢባን መስላችሁ በታያችሁ ነበር!

6 “የማቀርበውን ክርክር ስሙ፤ በደሌንም ስዘረዝር በጸጥታ አድምጡ።

7 በእግዚአብሔር ስም ስለምን ሐሰት ትናገራላችሁ? በማታለል እግዚአብሔርን የምታስደስቱ ይመስላችኋልን?

8 ለእርሱ ታደሉለታላችሁን? ለእርሱስ ጥብቅና ትቆማላችሁን?

9 እግዚአብሔር ቢመረምራችሁ አንዳች መልካም ነገር ያገኝባችኋልን? ሰዎችን እንደምታሞኙ እግዚአብሔርንም ማሞኘት የምትችሉ ይመስላችኋልን?

10 በስውር አድልዎ ብታደርጉ በእውነት እግዚአብሔር ይገሥጻችኋል።

11 ክብሩ አያስፈራችሁምን? ግርማውስ አያስደነግጣችሁምን?

12 ምሳሌያዊ አነጋገራችሁ እንደ ዐመድ ዋጋ ቢሶች ናቸው፤ ክርክራችሁም እንደ ሸክላ ተሰባብሮ ይወድቃል።

13 እስቲ ዝም በሉ እኔም እንድናገር ዕድል ስጡኝ ከዚያ በኋላ የፈለገው ነገር ይሁን።

14 “ጥርሴን ነክሼ ስጨነቅ የምኖረው ለምንድን ነው? ሕይወቴም በእጄ ላይ ነች።

15 ስለዚህ እግዚአብሔር ሊገድለኝ ቢፈልግ ምንም የሚቀርብኝ ነገር የለም፤ ሆኖም ሁኔታዬን ለእርሱ አስረዳለሁ።

16 ኃጢአተኛ ሰው በእግዚአብሔር ፊት መቅረብ ስለማይችል ምናልባት ይህ ድፍረቴ የመዳን ምክንያት ሊሆን ይችላል።

17 እስቲ የምናገረውን ቃል በጥንቃቄ አድምጡ የማቀርበውንም ማስረጃ ስሙ።

18 ክርክሬን በመልካም ሁኔታ አዘጋጅቼ አቅርቤአለሁ፤ እንደሚፈርድልኝም ዐውቃለሁ።

19 የሚከሰኝ ካለ፥ ሳልከራከር ጸጥ ብዬ እሞታለሁ።

20 ጌታ ሆይ! ከፊትህ እንዳልሰወር እነዚህን ሁለት ነገሮች አድርግልኝ፤

21 ይኸውም የቅጣት ክንድህን ከእኔ ላይ አንሣ፤ አስፈሪ በሆነው ግርማህ አታስደንግጠኝ።

22 “አምላክ ሆይ! አንተ በመጀመሪያ ተናገር፤ እኔም መልስ እሰጣለሁ፤ ወይም እኔ ልናገርና አንተ መልስ ስጠኝ።

23 ለመሆኑ የሠራሁት በደልና ኃጢአት ምን ያኽል ነው? እስቲ መተላለፌንና ኃጢአቴን አስታውቀኝ።

24 ፊትህን ከእኔ ሰውረህ እንደ ጠላት የቈጠርከኝ ስለምንድን ነው?

25 ነፋስ እንደሚያረግፈው ቅጠልና እንደ ደረቅ ገለባ ለምን በማስፈራራት ታሳድደኛለህ?

26 “በእኔ ላይ የጻፍከው ክስ እጅግ መራራ ነው፤ በልጅነቴ የሠራሁትን በደል እንኳ አልተውክልኝም፤

27 እግሮቼን በግንዶች መካከል አስረሃል፤ እያንዳንዱን እርምጃዬን ትቈጣጠራለህ፤ የእግሬን ዱካ ትመረምራለህ።

28 ከዚህ የተነሣ እኔ እንደ በሰበሰ ነገር ሆኜ እቀራለሁ፤ ብል እንደ በላውም ልብስ እጠፋለሁ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告