Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ኢዮብ

1 ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፦

2 “በእርግጥ እናንተ በጣም ብልኆች ናችሁ፤ ስትሞቱም ጥበብ ከእናንተ ጋር የምትሞት ይመስላችኋል!

3 ይሁን እንጂ እኔም የእናንተን ያኽል ማስተዋል አለኝ፤ ከቶ ከእናንተ በምንም አላንስም፤ እናንተ የተናገራችሁትን ሰው ሁሉ ያውቀዋል።

4 እግዚአብሔርን ጠርቼው የመለሰልኝ ጊዜ ነበር፤ አሁን እኔ የወዳጆቼ መሳቂያ ሆኛለሁ፤ ስሕተት የሌለብኝ ፍጹሙ እኔ የሰው ሁሉ መሳለቂያ ሆኛለሁ።

5 ችግር ባልደረሰበት ሰው ዘንድ የተቸገረን ሰው ችግር ማናናቅ ቀላል ነው። ነገር ግን ሊወድቅ የሚንገዳገደውን ሰው ትገፈትሩታላችሁ።

6 ኀይላቸውን እንደ አምላክ አድርገው የሚቈጥሩ ሌቦችና እግዚአብሔርን የካዱ ሰዎች እንኳ በሰላም ይኖራሉ።

7 “ነገር ግን እንስሶችን ጠይቅ ያስተምሩሃል፤ የሰማይንም ወፎች ጠይቅ ይነግሩህማል።

8 ወይም ለምድር ተናገር፤ እርስዋም ታስተምርሃለች፤ የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል።

9 ከእነዚህ ሁሉ መካከል የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንደ ሠራ የማያውቅ ማነው?

10 ሕይወት ያለው ፍጥረት ሁሉና የእያንዳንዱም ሰው ነፍስ በእግዚአብሔር ሥልጣን ሥር ነው።

11 ምላስ የምግብን ጣዕም ለይቶ እንደሚያውቅ፥ ጆሮም የንግግርን ዐይነት መርምሮ ይለያል።

12 “ጥበብ በሽምግልና፥ ማስተዋልም በዕድሜ መርዘም ይገኛሉ።

13 እግዚአብሔር ግን ጥበብና ኀይል አለው፤ ምክርና አስተዋይነት የሚገኙት ከእርሱ ነው።

14 እግዚአብሔር ያፈረሰውን ማንም መልሶ መሥራት አይችልም፤ እግዚአብሔር ያሰረውንም ማንም ሊፈታው አይችልም፤

15 እግዚአብሔር ዝናብን ቢከለክል ድርቅ ይሆናል፤ ዝናብን ቢለቅ ግን ምድር በጐርፍ ትጥለቀለቃለች።

16 እግዚአብሔር ብርቱና ድል አድራጊ ነው፤ የሚታለልም ሆነ የሚያታልል ሁለቱም በእርሱ ሥልጣን ሥር ናቸው።

17 እርሱ አማካሪዎችን ጥበብ ይነሣቸዋል፤ የሕዝብ መሪዎችንም ሞኞች ያደርጋቸዋል።

18 እርሱ ነገሥታትን ከዙፋናቸው ያወርዳል፤ ሽርጥ የታጠቁ እስረኞችም ያደርጋቸዋል።

19 ካህናትን ሥልጣናቸውን ገፎ ያባርራቸዋል፤ ባለሥልጣኖችን ከሥልጣናቸው ያስወግዳቸዋል።

20 የታመኑትን ሰዎች ዝም ያሰኛቸዋል፤ ከሽማግሌዎችም አስተዋይነትን ይነሣል።

21 መኳንንትን ያሳፍራቸዋል፤ የኀያላንን ኀይል ያስወግዳል።

22 በጨለማ የተሰወረውን ምሥጢር ይገልጣል፤ ድቅድቅ ጨለማን ወደ ብርሃን ይለውጣል።

23 መንግሥታትንም ታላላቅ ያደርጋቸዋል፤ ያጠፋቸዋልም፤ ሕዝብን ያበዛል፤ ይበታትናልም።

24 መሪዎች ማስተዋል እንዲጐድላቸውና መንገድ በሌለበት በበረሓ እንዲቅበዘበዙ ያደርጋል።

25 ብርሃን አጥተው በጨለማ እንዲደናበሩና እንደ ሰከረም ሰው እንዲንገዳገዱ ያደርጋቸዋል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告