ኢዮብ 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምጾፋር 1 ናዕማታዊውም ጾፋር እንዲህ አለ፦ 2 “ለዚህ ሁሉ ከንቱ ቃል መልስ የሚሰጥ የለምን? አንድ ሰው ይህን ያኽል በመለፍለፍ ትክክለኛ ሊሆን ይችላልን? 3 ኢዮብ ሆይ! ከንቱ ንግግርህ መልስ የማይሰጥበት ይመስልሃልን? ይህን ያኽልስ ስታፌዝ፥ የሚገሥጽህ የሌለ መሰለህን? 4 በሐሳብህ ‘ትክክለኛ ነኝ’ ትላለህ፤ ለእግዚአብሔርም ‘በፊትህ ንጹሕ ነኝ’ ትለዋለህ። 5 ምነው እግዚአብሔር በተናገረና ትክክለኛውን መልስ በሰጠህ! 6 የጥበብ መንገድ ብዙ ስለ ሆነ፥ ምነው ጌታ የጥበብን ምሥጢር ቢገልጥልህ! ስለዚህ እግዚአብሔር የቀጣህ፥ ከሚገባህ አሳንሶ መሆኑን ዕወቅ። 7 “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ምሥጢር ማወቅ ትችላለህን? ሁሉን ቻይ አምላክንስ መርምረህ ልትደርስበት ትችላለህን? 8 የእርሱ ታላቅነት ከሰማይ በላይ ነው፤ አንተ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ጥልቀቱም ከሲኦልም በታች ነው፤ አንተ ምን ታውቃለህ? 9 የእግዚአብሔር ታላቅነት ከምድር ይረዝማል፤ ከባሕርም ይሰፋል። 10 እግዚአብሔር መጥቶ ቢያስር፥ ወደ ፍርድ ሸንጎም ቢያቀርብ፥ ማን ይከለክለዋል? 11 እግዚአብሔር የማይጠቅሙ ሰዎችን ያውቃቸዋል፤ በደልን በሚያይበት ጊዜ ዝም ብሎ አይመለከትም። 12 ሞኝ ሰው ጥበበኛ ከሚሆን ይልቅ የሜዳ አህያ ሰው ሆኖ ቢወለድ ይቀላል። 13 “ሆኖም፥ ልብህን የቀና ብታደርግ እጅህንም ዘርግተህ ወደ እግዚአብሔር ብትጸልይ፥ 14 ኃጢአትን ከእጅህ ብታርቅ፥ ክፉ ነገርም በቤትህ እንዲገኝ ባታደርግ፥ 15 በዚያን ጊዜ ቀና ብለህ ያለ ኀፍረት ሁሉን ነገር ታያለህ፤ ያለ ፍርሀትም ጸንተህ መቆም ትችላለህ። 16 ችግርህን ሁሉ ትረሳዋለህ፤ የምታስታውሰውም እንዳለፈ ጐርፍ ብቻ ነው። 17 ሕይወትህ ከቀትር ፀሐይ ይበልጥ ይበራል፤ ጨለማው እንደ ማለዳ ብርሃን ይሆናል። 18 ተስፋ ስላለህ አንተም በመተማመን ትኖራለህ፤ እግዚአብሔር ስለሚጠብቅህ ያለ ስጋት ዐርፈህ ትኖራለህ። 19 ማንንም ሳትፈራ ትተኛለህ፤ ብዙ ሰዎችም በአንተ ፊት ሞገስ ማግኘትን ይፈልጋሉ። 20 የክፉዎች ዐይን ይታወራል፤ የማምለጫ መንገዳቸው ሁሉ የተዘጋ ነው፤ የእነርሱም መጨረሻ ሞት ነው።” |