Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 “መኖር ሰልችቶኛል፤ የማሳልፈውን መራራ ሕይወት በግልጽ አሰማለሁ።

2 እግዚአብሔርን እንዲህ እለዋለሁ፦ በእኔ ላይ ያለህን ቅርታ ግለጥልኝ እንጂ አትፍረድብኝ!

3 ይህን ያኽል ማስጨነቅህ አግባብ ነውን? አንተ ራስህ የፈጠርከውን ሰው መናቅ ይገባሃልን? የክፉ ሰዎችስ ሤራ ደስ ያሰኝሃልን?

4 የአንተ ዐይን እንደ ሰው ዐይን ነውን? ወይስ የምታየው እንደ ሰው ነውን?

5 የአንተ ቀኖች እንደ ሰው ቀኖች ናቸውን ወይስ ያንተ ዕድሜ እንደ ሰው ዕድሜ አጭር ነውን?

6 የእኔን በደል የምትመለከት፥ ኃጢአቴንም የምትከታተለው፥ ለምንድን ነው?

7 በደለኛ አለመሆኔንና ከአንተም እጅ ማንም ሊያድነኝ እንደማይችል አንተ ታውቃለህ።

8 “ቅርጽና መልክ ሰጥተው ያበጁኝ እጆችህ ናቸው፤ ታዲያ፥ አሁን እነዚያ እጆችህ መልሰው ያፈርሱኛልን?

9 እንደ ሸክላ ዕቃ ከዐፈር እንደ ሠራኸኝ አስብ፤ ታዲያ፥ አሁን መልሰህ እንደ ትቢያ ልታደቀኝ ነውን?

10 እንደ ወተት ፈሳሽ እንደ ዕርጎም አረጋኸኝ።

11 ሰውነቴን በቈዳና በሥጋ ሸፈንከው፥ በአጥንትና በጅማትም አገጣጠምከው።

12 ሕይወትንና ዘለዓለማዊ ፍቅርን ሰጥተኸኛል፤ ጥበቃህም መንፈሴን አጸናው።

13 ለካስ እነዚህን ነገሮች በልብህ ሰውረኻቸው ኖሮአል፤ ዓላማህም ይህ እንደ ሆነ ዐወቅሁ።

14 በደል ብፈጽም አንተ ትመለከታለህ፤ ኃጢአቴንም ሳትቀጣ አታልፈውም።

15 ኃጢአት ብሠራ ወዲያው ችግር ውስጥ እወድቃለሁ ደግ ነገር ብሠራም አልመሰገንም ተጐሣቊዬ ኀፍረት ደርሶብኛል።

16 ትዕቢት ቢሰማኝ እንደ አንበሳ አድነህ ትይዘኛለህ፤ እኔንም ለመጒዳት መላልሰህ ታደርጋለህ።

17 በእኔ ላይ የሚመሰክሩ ሰዎች ዘወትር ታገኛለህ፤ በእኔ ላይ የምታሳየው ቊጣ እያደገ ይሄዳል፤ እኔን ለማጥቃት ዘወትር አዳዲስ ዕቅዶችን እንደ ሠራዊት ታሰልፍብኛለህ።

18 “አምላክ ሆይ! ስለምን እንድወለድ አደረግኸኝ? ማንም ሳያየኝ ብሞት መልካም በሆነ ነበር!

19 ሳልፈጠር በቀረሁ፥ ከማሕፀንም በቀጥታ ወደ መቃብር ብወሰድ ኖሮ በተሻለኝ ነበር።

20 የሕይወቴ ዘመን አጭር አይደለምን? በዚህች አጭር ዘመን ጥቂት እንድደሰት እባክህ ተወኝ!

21 ይኸውም ዳግመኛ ወደማልመለስበት ጭፍግግ ወዳለውና ድቅድቅ ጨለማ ወደ ሆነው አገር ከመሄዴ በፊት ነው።

22 የምሄድበት ስፍራ የጨለማ ጥላና ሁከት የተሞላበት ምድር ነው፤ በዚያም ያለው ብርሃን እንደ ጨለማ ነው።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告