ኢሳይያስ 66 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ፈራጅነት 1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ ማሳረፊያ ናት፤ ታዲያ ለእኔ ምን ዐይነት ቤት ትሠሩልኛላችሁ? የማርፍበትስ ቦታ ምን ዐይነት ነው? 2 እነዚህን ሁሉ ነገሮች የፈጠርኩ እኔ ነኝ፤ ስለዚህ ሁሉም የእኔ ናቸው፤ እኔ የምመለከተው ልባቸው ወደ ተሰበረ፥ ትሑት መንፈስ ወዳላቸውና፥ ቃሌንም ወደሚያከብሩ ነው። 3 “ለእኔ በሬ ሲሠዉ በሌላ በኩል የሰውን ሕይወት ያጠፋሉ፤ ለእኔ ጠቦት ሲሠዉ ለጣዖትም ውሻ ያቀርባሉ፤ ለእኔ የእህል መሥዋዕት ሲያቀርቡ፤ የዕሪያ ደምም ለጣዖት ያቀርባሉ፤ ለእኔ ዕጣን ያጥናሉ፤ ጣዖቶቻቸውንም ያመሰግናሉ፤ የራሳቸውን አካሄድ በመምረጥ በርኲሰታቸው ይደሰታሉ። 4 ስጠራ ማንም ስላልመለሰልኝ፥ ስናገር ማንም ስላላዳመጠኝ ነገር በፊቴ ክፉ የሆነውን ነገር ስላደረጉና የማያስደስተኝን ስለ መረጡ እኔም በእነርሱ ላይ ቅጣት አመጣባቸዋለሁ።” 5 ቃሉን የምታከብሩ እናንተ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፦ “ስለ ስሜ የሚጠሉአችሁና የሚያገሉአችሁ እንዲህ ይሉአችኋል፦ ‘እናንተ ስትደሰቱ እናይ ዘንድ እስቲ እግዚአብሔር ክብሩን ይግለጥ፤’ ኀፍረት ላይ የሚወድቁት ግን እነርሱ ራሳቸው ናቸው። 6 በከተማ የሚሰማውን ሁካታ አድምጡ! ከቤተ መቅደስም ድምፅ ስሙ፤ ይህም እኔ እግዚአብሔር ለጠላቶቼ ተገቢ ዋጋቸውን በምሰጥበት ጊዜ የሚሰማ ድምፅ ነው።” 7 ጽዮን ምጥ ሳይጀምራት እንደ ወለደች፥ የምጥ ስሜት ሳይሰማት እንደ ተገላገለች ሴት ነች። 8 እንዲህ ያለ ነገር የሰማ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ያየ ማነው? አንድ አገር በአንድ ቀን፥ አንድ ሕዝብ በቅጽበት ሊወለዱ ይችላሉን? ይሁን እንጂ ጽዮን ምጥ እንደ ያዛት ወዲያውኑ ልጆችዋን ወልዳለች። 9 እግዚአብሔር አምላካችሁ እንዲህ ይላል፦ “የመውለጃዋ ጊዜ እንዲደርስ ያደረግኋትን ሴት ልጅዋን እንዳትወልድ አደርጋለሁን? እንድትፀንስ ያደረግኋትን ሴት ማሕፀኗን እዘጋለሁን? 10 የምትወዷት ሁሉ ከኢየሩሳሌም ጋር ደስ ይበላችሁ! ስለ እርስዋም ሐሴት አድርጉ! ያለቀሳችሁላት ሁሉ ስለ እርስዋ ተደሰቱ! 11 ይህንንም የምታደርጉት ከመጽናኛ ጡትዋ ጠብታችሁ ትጠግቡ ዘንድ፥ ከተከበረው ደረትዋ የተትረፈረፈውን ወተት ጠጥታችሁ ትደሰቱ ዘንድ ነው።” 12 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሀብትዋን እንደ ወንዝ ውሃ አበዛዋለሁ፤ የሕዝቦችንም ሀብት እንደ ወንዝ ጅረት አደርገዋለሁ፤ በክንድዋም ተይዛችሁ ትጠባላችሁ፤ በጭንዋም ላይ አድርጋ ትንከባከባችኋለች። 13 እናት ልጅዋን እንደምታጽናና እኔም እናንተን አጽናናችኋለሁ፤ በኢየሩሳሌምም ትጽናናላችሁ። 14 ይህም ሲፈጸም በምታዩበት ጊዜ ሐሴት ታደርጋላችሁ፤ ሰውነታችሁም እንደ ሣር ይለመልማል፤ የእግዚአብሔር ኀይል ከአገልጋዮቹ ጋር፥ ቊጣው ግን በሚጠሉት ላይ እንደሚሆን ይታወቃል።” 15 እግዚአብሔር በኀይለኛ ቊጣው ለመበቀልና በሚንበለበለው እሳት ለመገሠጽ በእሳት ሆኖ ይመጣል፤ መንኲራኲሮችም እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው። 16 እግዚአብሔር በሰዎች ሁሉ ላይ በእሳትና በሰይፍ ይፈርዳል፤ እንዲሁም በሞት የሚቀጣቸው ብዙዎች ናቸው። 17 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእርያ ሥጋና አይጥ፥ እንዲሁም ሌሎች አጸያፊ ነገሮች ከሚበሉት ሰዎች መካከል አንዱን ተከትለው ወደ አትክልቶቹ ቦታዎች ለመሄድ ራሳቸውን የሚለዩና የሚያነጹ በአንድነት ይጠፋሉ። 18 እኔ ሥራቸውንና ሐሳባቸውን ስለማውቅ የተለያየ ቋንቋ ያላቸውን ሕዝቦች ሁሉ እሰበስባለሁ፤ መጥተውም የእኔን ክብር ያያሉ። 19 በመካከላቸውም ምልክት አደርጋለሁ፤ ከሞት ከተረፉት መካከል ስለ እኔ ወዳልሰሙትና ክብሬንም ወዳላዩት ወደ ተለያዩ ሕዝቦች ወደ ተርሴስ፥ ወደ ሊብያውያን ቀስት ወደሚያስፈነጥሩ ወደ ሊድያውያን፥ ወደ ቱባል፥ ወደ ግሪክ፥ ራቅ ብለው ወደሚገኙት ደሴቶችም እልካቸዋለሁ፤ እነርሱም በሕዝቦች መካከል ክብሬን ይገልጣሉ። 20 ወንድሞቻችሁን ሁሉ ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቅዱስ ተራራዬ በፈረሶች፥ በሠረገሎች፥ በጋሪዎች፥ በበቅሎዎችና በግመሎች አድርገው ከተለያዩ አገሮች ለእግዚአብሔር እንደ መባ ያመጡአቸዋል፤ እነርሱንም የሚያመጡአቸው እስራኤላውያን የእህል ቊርባንን በሥርዓት በነጻ ዕቃ ለእኔ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሚያቀርቡ አድርገው ነው፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 21 እኔም ከእነርሱ አንዳንዶቹን ካህናትና ሌዋውያን ሆነው እንዲያገለግሉ አደርጋቸዋለሁ። 22 “የምፈጥራቸው አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር በእኔ ጸንተው እንደሚኖሩ እንዲሁም ዘራችሁና ስማችሁ በእኔ ጸንተው ይኖራሉ፤ 23 ከወር መባቻ እስከ ሌላ የወር መባቻ በዓልና ከሰንበት እስከሚቀጥለው ሰንበት ሕዝብ ሁሉ በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ሊሰግዱልኝ ይመጣሉ”፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 24 “ወጥተው ሲሄዱም በእኔ ላይ በማመፃቸው የተገደሉትን ሰዎች በድን ያያሉ፤ እነርሱን የሚበላቸው ትል አይሞትም፤ የሚያቃጥላቸውም እሳት አይጠፋም፤ እነርሱንም የሚያያቸው የሰው ዘር ሁሉ ይጸየፋቸዋል።” |