Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 64 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 ምነው ሰማያትን ከፍተህ ብትወርድ፤ ተራራዎችም አንተን አይተው ምነው በተንቀጠቀጡ፤

2 እሳት ደረቁን እንጨት በሚያጋይ ጊዜ ፍሙ የተጣደውን ውሃ እንደሚያፍለቀልቀው፥ ሕዝቦችም በአንተ መገለጥ እንዲንቀጠቀጡ ወርደህ ስምህ በጠላቶችህ ዘንድ እንዲታወቅ አድርግ!

3 ከዚህ በፊትም መጥተህ እኛ ያልጠበቅናቸውን እጅግ አስፈሪ የሆኑ ነገሮችን በፈጸምክበት ጊዜ ተራራዎች አንተን አይተው በፍርሃት ተንቀጠቀጡ።

4 ከጥንት ጀምሮ ተስፋቸውን በእርሱ አድርገው ለሚተማመኑበት ወገኖች እነዚያን ሁሉ ድንቅ ነገሮች ያደረገ አምላክ ከአንተ በቀር አልተሰማም፤ አልታየም፤ የተረዳም የለም።

5 የአንተን መንገድ አስታውሰው ፈቃድህን በደስታ የሚፈጽሙትን ትረዳቸዋለህ፤ ፈቃድህን መተላለፍን በቀጠልን ጊዜ ግን አንተ ተቈጣኸን፤ ታዲያ እንዴት ልንድን እንችላለን?

6 እኛ ሁላችን በኃጢአት ረክሰናል፤ ጽድቃችንም እንደ አደፍ ጨርቅ ሆኖአል፤ ከኃጢአታችን ብዛት የተነሣ ደርቀው በነፋስ እንደሚረግፉ ቅጠሎች ሆነናል።

7 በኃጢአታችን ምክንያት ፊትህን ስላዞርክብንና ለበደላችንም ተገዢዎች እንድንሆን ስለ ተውከን ስምህን የሚጠራና አንተን ለማግኘት የሚጥር ማንም የለም።

8 ሆኖም አምላክ ሆይ! አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ሸክላዎች ስንሆን አንተ ሠሪአችን ነህ፤ ሁላችንም የእጅህ ሥራ ነን።

9 አምላክ ሆይ! አምርረህ አትቈጣ፤ ኃጢአታችንንም ለዘለዓለም አታስብብን፤ እኛ ሁላችን ሕዝብህ መሆናችንን አስታውስ።

10 የተቀደሱ ከተሞችህ በረሓ ሆነዋል፤ ጽዮን በረሓ ኢየሩሳሌምም ባድማ ሆነዋል።

11 የቀድሞ አባቶቻችን አንተን ሲያመሰግኑበት የነበረ፥ ቅዱስና ውብ የሆነው ቤተ መቅደስህ በእሳት ጋይቶአል፤ የሚያስደስቱ ነገሮች ሁሉ ፈራርሰዋል።

12 አምላክ ሆይ! ከዚህ ሁሉ በኋላ አንዳች ነገር አታደርግምን? ዝም ብለህስ በኀይለኛ ቅጣት ትቀጣናለህን?

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告