Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 63 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእግዚአብሔር ድልና የማዳን ኀይሉ

1 ከኤዶም ቦጽራ ቀይ መጐናጸፊያ ተጐናጽፎ የሚመጣው ይህ ማነው? በታላቅ ኀይሉ አስደናቂ ልብስ ለብሶ የሚራመደው ይህ ማነው? “ፍርድን የምሰጥ የማዳን ኀይል ያለኝ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”

2 “የወይን ጠጅ ጨምቆ ለማውጣት የወይን ፍሬ ሲጨምቅ እንደ ነበረ ሰው ልብስህ ስለምን ቀይ ሆነ?”

3 እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ይመልሳል “እኔ ብቻዬን አሕዛብን ሁሉ እንደ ወይን ረገጥኩ፤ ይህን በማደርግበት ጊዜ ከሕዝቦች ከእኔ ጋር ማንም አልነበረም፤ እኔ በቊጣዬ ረገጥኳቸው፤ በመዓቴም አደቀቅኋቸው፤ ደማቸውም በልብሴ ላይ ተረጨ።

4 የምበቀልበትን ጊዜ ወስኜአለሁ፤ ሕዝቤን የምታደግበትም ጊዜ ደርሶአል።

5 ዙሪያዬን በተመለከትኩ ጊዜ የሚረዳ ማንም አልነበረም። ደጋፊ ባለመኖሩ ተደነቅሁ፤ ስለዚህ በኀይለኛ ቊጣዬ አማካይነት እኔው ራሴ ድልን አመጣሁ።

6 ሰዎችን በቊጣዬ ረግጬ ጣልኳቸው፤ ኀይለኛ ቊጣዬ እንዲሰማቸው አደረግሁ፤ ደማቸውንም በምድር ላይ አፈሰስኩ።”


እግዚአብሔር ለእስራኤል ያሳየው ቸርነት

7 ለእኛ ስላደረጋቸው ድርጊቶች ሁሉ፥ ለእስራኤል ሕዝብ እንደ መሐሪነቱ ስላሳየው ከፍተኛ በጎ አመለካከት፥ ስለ ተትረፈረፈውም ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የእግዚአብሔርን ቸርነት ምስጉን ድርጊቶቹን እዘረዝራለሁ።

8 እግዚአብሔር “በእርግጥ እነርሱ የእኔ ወገኖችና የማይዋሹ ልጆች ናቸው” አለ። ለእነርሱም አዳኛቸው ሆነ።

9 በችግራቸው ጊዜ ሁሉ ያዳናቸው በመልእክተኛ ወይም በመልአክ አማካይነት ሳይሆን እርሱ በመካከላቸው በመገኘት ነው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ታደጋቸው፤ እርሱም በቀድሞ ዘመናት ሁሉ አንሥቶ ልጁን እንደሚሸከም ሰው ተንከባከባቸው።

10 ሆኖም እነርሱ የእርሱን ቅዱስ መንፈስ አሳዘኑ፤ ስለዚህ እሱ በእነርሱ ላይ ተነሥቶ ቀጣቸው።

11 ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ የነበረበትን የቀድሞውን ዘመን ማስታወስ ጀመሩ፤ ከመንጋዎቹ እረኞች ጋር ከባሕር ያወጣቸው እግዚአብሔር የት አለ? ቅዱስ መንፈሱን በውስጣቸው ያሳደረው እግዚአብሔር የት ነው?

12 ለራሱ ዘለዓለማዊ ስም ይሆን ዘንድ በፊታቸው ውሃን ለመክፈል ክብርን የተመላ ኀይሉን በሙሴ ቀኝ በኩል እንዲራመድ ያደረገው የት አለ?

13 በጥልቁ ሲሄዱ እንዳይሰናከሉ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ እንዳለ ፈረስ አደረጋቸው።

14 እንዲሁም በሸለቆው ውስጥ እንደሚሄድ የከብት መንጋ የእግዚአብሔር መንፈስ ዕረፍትን ሰጣቸው። ስምህ ይከብር ዘንድ ሕዝብህን በዚህ ዐይነት መራሃቸው።


ምሕረትንና ርዳታን ለማግኘት የቀረበ ጸሎት

15 እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ከተቀደሰውና ከክቡር መኖሪያህ ከሰማይ ወደ ታች ተመልከት፤ ቅንአትህና ኀይልህ የት አሉ? መልካም ፈቃድህና ርኅራኄህስ የት አለ? እነርሱ ከእኛ ርቀዋል።

16 አብርሃም ባያውቀን፥ እስራኤል ባይቀበለንም እንኳ አንተ አባታችን ነህ፤ አምላክ ሆይ! ስምህ ከጥንት እንደ ሆነ ሁሉ አንተ አባታችን ነህ፤ አንተ ታዳጊአችን ነህ።

17 አምላክ ሆይ! ለምን መንገድህን እንድንስት አደረግኸን? እንዳንፈራህስ ለምን ልባችንን አደነደንክ? ለአገልጋዮችህ፥ የአንተ ስለ ሆኑት ነገዶች ስትል እባክህ ተመለስ።

18 ለጥቂት ጊዜ ቤተ መቅደስህ የቅዱስ ሕዝብህ ንብረት ነበር፤ አሁን ግን ጠላቶቻችን ረገጡት።

19 እኛ በአንተ እንዳልተገዙና በስምህ እንዳልተጠሩ ወገኖች ከሆንን ብዙ ጊዜአችን ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告