ኢሳይያስ 62 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 የሚሰጣት ፍርድ እንደ ንጋት እስኪፈነጥቅና መዳንዋም እንደሚነድ ችቦ እስኪበራ ድረስ፥ ስለ ጽዮን ዝም አልልም፤ ስለ ኢየሩሳሌምም ከማሰብ አላርፍም። 2 ሕዝቦች የሚሰጥሽን ፍርድ፥ ነገሥታትም ክብርሽን ያያሉ፤ አንቺም እግዚአብሔር በሚያወጣልሽ አዲስ ስም ትጠሪአለሽ። 3 አንቺ በእግዚአብሔር እጅ እንዳለው የተዋበ አክሊልና በአምላክሽም እጅ እንዳለው የነገሥታት ዘውድ ትሆኚአለሽ። 4 ከእንግዲህ ወዲህ “የተተወች” ተብለሽ አትጠሪም፤ ምድርሽም “ባድማ” ተብላ አትጠራም። የምትጠሪበትም አዲስ ስም፥ “እግዚአብሔር በእርስዋ ደስ ይለዋል!” የሚል ይሆናል፤ ምድርሽም “ባለ ባል” ተብላ ትጠራለች፤ እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤ ምድርሽም ባል እንዳላት ሴት ትሆናለች። 5 ጐልማሳ ድንግሊቱን ሙሽራ አድርጎ እንደሚወስድ፥ የፈጠረሽ እግዚአብሔርም ለአንቺ እንደ ባል ይሆንልሻል፤ ወንዱም ሙሽራ በሴትዋ ሙሽራ ደስ እንደሚሰኝ፥ እግዚአብሔርም በአንቺ ደስ ይለዋል። 6 ኢየሩሳሌም ሆይ! በቅጥሮችሽ ላይ ቀንና ሌሊት ዝም የማይሉ ጠባቂዎችን አኑሬአለሁ፤ እናንተ እግዚአብሔርን የምትለምኑ ዕረፍት አታድርጉ። 7 ኢየሩሳሌምን እስኪመሠርታትና በምድር ሁሉ ዝነኛ ከተማ እስከሚያደርጋት ድረስ ሳታቋርጡ አሳስቡት። 8 እግዚአብሔር በኃይሉና በሥልጣኑ እንዲህ ሲል ማለ፦ “ከእንግዲህ ወዲያ እህልሽን ጠላቶችሽ እንዲበሉት አላደርግም፤ የደከምሽበትን አዲስ የወይን ጠጅሽንም ባዕዳን እንዲጠጡት አላደርግም። 9 ነገር ግን በጐተራ የሰበሰቡትን እህል እነርሱ ራሳቸው በልተው እኔ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፤ የሰበሰቡትንም የወይን ዘለላ የወይን ጠጅ እነርሱ ራሳቸው በተቀደሰ አደባባዬ ይጠጡታል። 10 በቅጥር በሩ በኩል ዕለፉ፤ ለሰዎች መንገዱን አዘጋጁ፤ አውራ ጐዳናውን ሥሩ፤ ድንጋዮችን አስወግዱ፤ አርማውንም ለሕዝቦች ከፍ አድርጉ።” 11 እግዚአብሔር ለዓለም ሁሉ እንዲህ ብሎ ያውጃል፦ “አዳኝሽ ይመጣል፤ ከእርሱም ጋር ለሰዎች የሚከፍለው ዋጋና ሽልማት አለ ብላችሁ ለጽዮን ልጅ ንገሩአት።” 12 ሕዝቡ “የተቀደሱና እግዚአብሔር የታደጋቸው ወገኖች” ተብለው ይጠራሉ፤ አንቺም ኢየሩሳሌም “የተፈለገችና ያልተተወች ከተማ” ተብለሽ ትጠሪአለሽ። |