Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 60 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የወደፊቱ የኢየሩሳሌም ክብር

1 ኢየሩሳሌም ሆይ! ብርሃንሽ ስለ መጣ ተነሺና አብሪ፤ የእግዚአብሔርም ክብር በአንቺ ላይ ያበራል።

2 እነሆ፥ ጨለማ ምድርን፥ ድቅድቅ ጨለማም ሕዝብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በአንቺ ላይ ያበራል፤ ክብሩም በአንቺ ላይ ይገለጣል።

3 ሕዝቦች ወደ ብርሃንሽ፥ ነገሥታትም ወደ ንጋትሽ ወገግታ ይመጣሉ።

4 ቀና ብለሽ በዙሪያሽ ያለውን ሁኔታ ተመልከቺ! ሁላቸውም ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ አገር ይመጣሉ፤ ሴቶች ልጆችሽም በሞግዚቶቻቸው ክንድ ሆነው ወደ አንቺ ይመጣሉ።

5 ይህንንም አይተሽ ፈገግታሽ በደስታ ይፈካል፤ ከባሕር የሚገኘው በረከትና፥ ከሕዝቦች የሚመጣው ሀብት የአንቺ ስለሚሆን፥ ከደስታሽ ብዛት የተነሣ ልብሽ ይፈነድቃል።

6 ከምድያምና ከኤፋ የመጡት ግመሎች ምድራችሁን ሞሉት። ወርቅና ዕጣን ይዘው ከሳባ የመጡት ሁሉ እግዚአብሔርን በከፍተኛ ድምፅ ያመሰግኑታል።

7 የቄዳር የበግ መንጋዎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ፤ የነባዮት አውራ በጎችም ለመሥዋዕትነት ያገለግሉሻል፤ በመሠዊያም ላይ ለመሥዋዕትነት ለመቅረብ ተቀባይነት ይኖራቸዋል። የተከበረውን ቤተ መቅደሴንም አስጌጣለሁ።

8 እነዚህ እንደ ደመናና፥ ወይም ወደ ጎጆአቸው እንደሚመለሱ ርግቦች የሚያንዣብቡ እነማን ናቸው?

9 የእስራኤል ቅዱስ፥ እግዚአብሔር አምላካችሁ እናንተን ስላከበራችሁ ለእርሱ ክብር ሲሉ በተርሴስ መርከቦች መሪነት ልጆቻችሁን ከብራቸውና ከወርቃቸው ጋር ከሩቅ ቦታ ለማምጣት ደሴቶቹ እኔን ይጠባበቃሉ።

10 እኔ በቊጣዬ ቀጥቼሽ ነበር፤ አሁን ግን እራራልሻለሁ። ባዕዳን ሕዝቦች ቅጽሮችሽን ይሠራሉ፤ ንጉሦቻቸውም ያገለግሉሻል።

11 የሕዝቦችን፥ ሀብትና ንጉሦቻቸውን ያመጡ ዘንድ በሮችሽ ሌሊትና ቀን ክፍት ይሆናሉ እንጂ አይዘጉም።

12 አንቺን የማያገለግሉ ሕዝቦችና መንግሥቶች ግን ፈጽመው ይጠፋሉ።

13 ቤተ መቅደሴ ያረፈበትን ቦታ ለማስዋብ የሊባኖስ ግርማ የሆኑት ዝግባ አስታና ጥድ ወደ አንቺ እንዲመጡ ይደረጋሉ፤ እኔም የእግሬ ማረፊያ የሆነውን አከብረዋለሁ።

14 የጨቋኞችሽ የልጅ ልጆች ወደ አንቺ ሲመጡ እጅ ይነሣሉ፤ የናቁሽም ሁሉ በእግርሽ ሥር ይንበረከካሉ፤ እነርሱም አንቺን “የእስራኤል ቅዱስ የእግዚአብሔር ከተማ የሆነችው ጽዮን” ብለው ይጠሩሻል።

15 “ከዚህ በፊት የተተውሽና የተጠላሽ ሆነሽ ማንም በአንቺ በኩል የማያልፍ የነበረ ቢሆንም እንኳ፥ የዘለዓለም መመኪያና በየትውልዱ ሁሉ መደሰቻ እንድትሆኚ አደርግሻለሁ።

16 ልጆች የእናታቸውን ጡት እንደሚጠቡ የአንቺም ልጆች የሕዝቦችንና የነገሥታትን ሀብት በመውሰድ ይጠቀሙበታል፤ አንቺም እኔ እግዚአብሔር አዳኝሽና ታዳጊሽ ኀያሉ የያዕቆብ አምላክ መሆኔን ታውቂአለሽ።

17 “እኔ በነሐስ ፈንታ ወርቅ፥ በብረት ፈንታ ብር፥ በእንጨት ፈንታ ነሐስ፥ በድንጋይም ፈንታ ብረት አመጣለሁ፤ ሰላምን እንደ አስተዳዳሪሽ ጽድቅንም እንደ ገዢሽ አድርጌ እመድባለሁ።

18 ከእንግዲህ ወዲህ በምድርሽ የዐመፅ ድምፅ በድንበሮችሽም ጥፋት ወይም ውድመት አይሰማም፤ ነገር ግን ቅጥሮችሽን መዳን የቅጥር በሮችሽን ምስጋና ብለሽ ትጠሪአቸዋለሽ።

19 “ከእንግዲህ ወዲህ ፀሐይ በቀን፥ ጨረቃም በሌሊት አያበሩልሽም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ብርሃንሽ፥ አምላክሽም ክብርሽ ይሆናል።

20 እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ብርሃንሽ ስለሚሆን፥ ፀሐይሽ ከቶ አትጠልቅም፤ ጨረቃሽም ብርሃንዋን አትከለክልም፤ የመከራሽም ዘመን ያበቃል።

21 ሕዝብሽ ጻድቃን ይሆናሉ፤ ምድሪቱን ለዘለዓለም ይወርሳሉ፤ እኔ እመሰገን ዘንድ እነርሱን የፈጠርኳቸውና የተካኋቸው እኔ ነኝ።

22 ከእነርሱ ጥቂቶቹ በሺህ የሚቈጠር ብዛት ይኖራቸዋል፤ ከእነርሱም ደካሞች የነበሩት ኀያል ሕዝብ ይሆናሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ጉዳይ በጊዜው ፈጥኖ እንዲፈጸም አደርጋለሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告