ኢሳይያስ 56 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየሚታዘዙ ሁሉ ደኅንነትን እንደሚያገኙ 1 እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ይላል፦ “የማድንበት ጊዜ ፈጥኖ ስለሚመጣና እኔ የምታደግበትም ጊዜ ስለ ቀረበ ፍትሕን ጠብቁ ትክክለኛውንም ነገር አድርጉ። 2 ይህን የሚያደርግ፥ አጥብቆ የሚይዘው፥ ሰንበትን ሳይሽር የሚጠብቅ፥ እጁንም ክፉ ነገር ከማድረግ የሚገታ ሰው የተባረከ ነው።” 3 ወደ እግዚአብሔር የተጠጋ ባዕድ ሰው “እግዚአብሔር ከራሱ ሕዝብ ይለየኛል” ብሎ አያስብ፤ ጃንደረባ የሆነ ሰው ልጅ ባለመውለዱ፦ “እንደ ደረቅ ዛፍ ነኝ” አይበል። 4 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሰንበቴን ለሚያከብሩ፥ እኔ የምፈቅደውን ነገር ለሚመርጡና፥ በቃል ኪዳኔ ለሚጸኑ ጃንደረቦች 5 ለእነርሱ በቤተ መቅደሴና በግቢዬ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የተሻለ መታሰቢያ እንዲኖራቸው አደርጋለሁ፤ የማይረሳ ዘላቂ መታወቂያም እሰጣቸዋለሁ።” 6 ከባዕድ አገር መጥተው፥ ወደ እግዚአብሔር በመጠጋት እርሱን የሚወዱትንና የሚያገለግሉትን፥ የእርሱን ሰንበት ሳይሽሩ በማክበር ቃል ኪዳኑን የሚጠብቁትን ባዕዳንን እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፦ 7 “እነርሱን ወደ ተቀደሰው ተራራዬ አምጥቼ በጸሎት ቤቴም ደስ እንዲላቸው አደርጋለሁ፤ በመሠዊያዬም ላይ የሚያቀርቡትን የሚቃጠልና ሌሎችን መሥዋዕቶች ሁሉ እቀበላለሁ፤ ይህንንም የማደርገው ቤቴ የሕዝቦች ሁሉ ጸሎት ቤት ተብሎ ስለሚጠራ ነው።” 8 የተበተኑትን እስራኤላውያንን የሚሰበስበው ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከተሰበሰቡት ሌላ ሌሎችንም ወገኖች ወደ እነርሱ ሰብስቤ አመጣቸዋለሁ።” የእስራኤል መሪዎች መወገዝ 9 የባዕድ አገር ሕዝቦች እንደ አራዊት እየፈነጩ መጥተው ሕዝቡን ይውጡ ዘንድ እግዚአብሔር አዞአቸዋል፤ እርሱም እንዲህ ይላል፦ 10 “የእስራኤል ጠባቂዎች ዕውሮች ናቸው፤ ሁሉም ዕውቀት የላቸውም፤ እነርሱም፥ እንደሚያንቀላፉ፥ እንደሚጋደሙ፥ እንደሚያልሙና መጮኽ እንደማይችሉ ውሾች ናቸው። 11 እነርሱ በልተው እንደማይጠግቡ ውሾች ናቸው። የማያስተውሉም እረኞች ናቸው፤ ሁሉም በየራሳቸው መንገድ ይሄዳሉ፤ እያንዳንዱም የራሱን ጥቅም ያሳድዳል። 12 እነርሱም፦ ‘ኑ ወይን ጠጅ እንፈልግ በጠንካራ መጠጥም እንርካ! ነገም እንደ ዛሬ ይሆናል፤ እንዲያውም በጣም የተሻለ ይሆናል!’ ይላሉ!” |