Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 50 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ወንድ ሚስቱን ፈቶ እንደሚያባርር እኔ እናንተን ሕዝቤን ያባረርኩ ይመስላችኋልን? ይህስ ከሆነ የፍችው ደብዳቤ የት አለ? ሰው ልጆቹን ለባርነት እንደሚሸጥ እኔም እናንተን ለምርኮ አሳልፌ የሸጥኳችሁ ይመስላችኋልን? ከሆነስ ለማንኛውም አበዳሪዬ ሸጥኳችሁ? እናንተ ለምርኮ የተሰጣችሁት በኃጢአታችሁ ምክንያት ነው፤ የተሰደዳችሁትም በፈጸማችሁት በደል ነው።

2 “እኔ በመጣሁ ጊዜ ማንም ሰው አለመኖሩ ለምንድን ነው? በጠራሁም ጊዜ ማንም ሰው መልስ ያልሰጠኝ ለምንድን ነው? እኔ ለመታደግ አልችልምን? ለማዳንስ ኀይል የለኝምን? በተግሣጼ ብቻ ባሕርን አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ወደ ምድረ በዳነት እለውጣለሁ፤ ዓሣዎቻቸውም ውሃ ከማጣት የተነሣ ሞተው ይበሰብሳሉ።

3 ሰማያትን ጨለማ አለብሳቸዋለሁ መጋረጃቸውም ማቅ ይሆናል።”

4 ደካሞችን በቃል ማጽናትን ዐውቅ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር የምሁርን አንደበት ሰጥቶኛል፤ በየማለዳው ከእንቅልፍ ያነቃኛል፤ እንደ ተማሪም አዳምጥ ዘንድ ጆሮዬን ይከፍታል።

5 ጌታ እግዚአብሔር ማስተዋልን ሰጥቶኛል፤ እኔም ዐመፀኛ ሆኜ ከእርሱ አልራቅሁም።

6 ለሚገርፉኝ ጀርባዬን፥ ጢሜንም ለሚነጩ ጒንጬን ሰጠኋቸው፤ ከሚሰድቡኝና ከሚተፉብኝ ፊቴን አላዞርኩም።

7 ጌታ እግዚአብሔር ስለሚረዳኝ አልተዋረድኩም፤ ራሴን እንደ ጠንካራ ድንጋይ አበረታሁ፤ እንደማላፍርም ዐውቃለሁ።

8 የሚፈርድልኝ እግዚአብሔር ቅርብ ነው፤ ታዲያ ማን ይከሰኛል? የሚከሰኝ ካለ ፊት ለፊት እንገናኝ፤ እስቲ ይቋቋመኝ።

9 የሚረዳኝ ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ ማን ይፈርድብኛል? ከሳሾቼ እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ ብልም ይበላቸዋል።

10 ከእናንተ መካከል እግዚአብሔርን የሚፈራና ለአገልጋዩ ቃል የሚታዘዝ ማነው? ብርሃን የሌለው በጨለማ የሚመላለስ በእግዚአብሔር ይታመን፤ እምነቱንም በአምላኩ ላይ ይጣል።

11 እናንተ ሁላችሁም ነገር በሰው ላይ እንደ እሳት የምታነዱና እንደ ችቦ የምትለኲሱ ናችሁ፤ ባነደዳችሁት እሳት ነበልባል ውስጥና በለኰሳችሁት ችቦ ትጠፋላችሁ ይህንንም ቅጣት የምትቀበሉት ከእኔ ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告