ኢሳይያስ 48 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእግዚአብሔር ፈጣሪነትና አዳኝነት 1 በእስራኤል ስም የምትጠሩ፥ ከይሁዳ ወገን የሆናችሁ፥ እናንተ የያዕቆብ ልጆች! ይህን ስሙ። እናንተ በታማኝነትና በእውነት ሳይሆን፥ የእስራኤልን አምላክ እናመልካለን ትላላችሁ፤ በእግዚአብሔር ስምም ትምላላችሁ። 2 ራሳችሁም “የቅድስቲቱ ከተማ ነዋሪዎች ነን፤ በሠራዊት ጌታ በእስራኤል አምላክ እንተማመናለን” ብላችሁ ትመካላችሁ። 3 እግዚአብሔር ለእስራኤል እንዲህ ይላል፦ “ወደ ፊት ስለሚሆነው ነገር ከብዙ ጊዜ በፊት ተናገርኩ፤ እርሱንም በፍጥነት እንዲከናወን አደረግሁ። 4 እንደማይተጣጠፍ ነሐስና እንደ ጠንካራ ብረት የማትመለሱ እልኸኞች መሆናችሁን ዐውቃለሁ። 5 ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ፤ ከመፈጸማቸውም በፊት አስታውቄአችኋለሁ፤ ይህንንም ያደረግኹት ‘ጣዖቶቻችን ይህን አደረጉ፤ የእንጨትና የብረት ምስሎቻችን ይህን ወሰኑ’ እንዳትሉ ነው። 6 “እኔ የተናገርኩትን ሰምታችኋል፤ ይህም መፈጸሙን አይታችኋል፤ አስተውሉትና እውነተኛነቱን አረጋግጡ፤ ከአሁን ጀምሮ ቀድሞ ተሰውሮ የነበረ እናንተ ያላወቃችሁትን አዲስ ነገር ወደፊት አሳያችኋለሁ። 7 እነርሱ ከብዙ ጊዜ በፊት ሳይሆን አሁን የተፈጠሩ ናቸው፤ እናንተም ‘ቀደም ብለን ዐውቀናቸዋል’ እንዳትሉ ከአሁን በፊት ከቶ አልሰማችኋቸውም። 8 እኔ የምናገረውን አትሰሙም፤ ለማወቅም አትፈልጉም፤ ከጥንት ጀምሮ ጆሮአችሁ የተደፈነ ነው፤ ይህም የሆነው እናንተ በጣም ከዳተኞች መሆናችሁንና ከተወለዳችሁ ጀምሮ ዐመፀኞች ተብላችሁ መጠራታችሁን ዐውቃለሁ። 9 “ስለ ስሜ ክብር ቊጣዬን አዘገያለሁ፤ ሰዎችም ያመሰግኑኝ ዘንድ ቊጣዬ እንዳያጠፋችሁ እገታዋለሁ። 10 እንደ ብር ሳይሆን በመከራ እሳት አንጥሬአችኋለሁ፥ በችግር እቶንም ፈትኜአችኋለሁ። 11 ስለ እኔ ስለ ራሴ ይህን አደርገዋለሁ፤ ስሜስ ለምን ይነቀፋል? ክብሬንም ለማንም አልሰጥም።” እግዚአብሔር የመረጠው አገልጋይ 12 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የጠራኋችሁ የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ሆይ! አድምጡ! እኔ ብቻ አምላክ ነኝ፤ እኔ የመጀመሪያውና የመጨረሻው ነኝ። 13 እኔ ምድርን መሠረትኩ፤ ሰማያትንም ዘረጋሁ። ስጠራቸውም ይገኛሉ። 14 “ሁላችሁም ተሰብስባችሁ ኑና አድምጡ! ስለ እነዚህ ነገሮች አስቀድሞ የተናገረ ከጣዖቶች መካከል የትኛው ነው? የእግዚአብሔር ተመራጭ በባቢሎን ላይ ዓላማውን ይፈጽማል። ኀይሉም በባቢሎናውያን ላይ ይሆናል። 15 እኔ ራሴ ተናግሬአለሁ፤ ጠርቼዋለሁም፤ እኔ አመጣዋለሁ፤ የእርሱም ተልእኮ የተሳካ ይሆናል። 16 ወደ እኔ ቀርባችሁ ይህን ስሙ፤ ከመጀመሪያ ጀምሮ የተናገርኩት በምሥጢር አይደለም፤ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ እኔ እዚያ ነበርኩ።” አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል። 17 እናንተን የሚያድን የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል፤ “የሚጠቅምህን ሁሉ የማስተምርህና ልትሄድበት የሚገባህን መንገድ የምመራህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። 18 “ትእዛዞቼን በጥንቃቄ ሰምታችሁ ቢሆንማ ኖሮ፥ በረከታችሁ እንደማይደርቅ የወንዝ ውሃ፥ ጽድቃችሁም እንደ ባሕር ሞገድ በብዛት በመጣላችሁ ነበር! 19 ሕዝባችሁም ባልተደመሰሰና ስማችሁም ባልተረሳ ነበር!” 20 እንግዲህ ከባቢሎን ወጥታችሁ ሽሹ፤ “እግዚአብሔር አገልጋዩን እስራኤልን አድኖአል” የሚለውን የምሥራች ቃል በደስታ አብሥሩ፤ በየስፍራውም እንዲታወቅ አድርጉ። 21 እግዚአብሔር በምድረ በዳ በመራቸው ጊዜ ውሃ አልጠማቸውም፤ ይልቁንስ ውሃ ከአለት እንዲፈልቅላቸው አደረገ። አለቱን ከፍሎ ውሃ አጐረፈላቸው። 22 “ለክፉዎች ሰላም የላቸውም” ይላል እግዚአብሔር። |