ኢሳይያስ 47 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበባቢሎን ላይ የሚመጣ ፍርድ 1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “አንቺ በማንም ያልተደፈርሽ የባቢሎን ከተማ ሆይ! ወርደሽ በዐቧራ ላይ ተቀመጪ፤ ወርደሽ በዙፋን ላይ ሳይሆን፤ በመሬት ላይ ተቀመጪ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ቅምጥልና ለስላሳ መባልሽ ይቀራል። 2 እንግዲህ መጅ አንሥተሽ ዱቄት ፍጪ፤ ዐይነ ርግብሽን ግለጪ፤ ካባሽን አውልቂ፤ ቀሚስሽን ከፍ አድርገሽ በተራቈተ ቅልጥም ወንዙን ተሻገሪ። 3 ሕዝብ ሁሉ ተራቊተሽ ያዩሻል፤ ኀፍረትሽ ይጋለጣል፤ እኔ ማንንም ሳልምር ሁሉን እበቀላለሁ።” 4 አዳኛችን የሠራዊት አምላክ ነው፤ ስሙም የእስራኤል ቅዱስ ነው። 5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ባቢሎን ሆይ! በጨለማ ውስጥ ጸጥ ብለሽ ተቀመጪ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ‘የመንግሥታት ንግሥት’ ብለው አይጠሩሽም፤ 6 እኔ በሕዝቤ ላይ ተቈጥቼ ነበር፤ እነርሱንም እንደ ርኩስ ቈጥሬ፥ ለአንቺ አሳልፌ ሰጠኋቸው፤ አንቺ ግን ርኅራኄ አላደረግሽላቸውም፤ በዕድሜ በገፉት ሰዎች ላይ የጭቈና ቀንበር አበዛሽባቸው። 7 ‘እኔ ለዘለዓለም ንግሥት ሆኜ እኖራለሁ’ አልሽ፤ ስላደረግሽው ድርጊት ምንም አላሰብሽም፤ የተግባርሽም ውጤት ምን እንደሚሆን አላስተዋልሽም። 8 “አንቺ በልብሽ ‘እንደ እኔ ያለ ማንም የለም፤ ባልዋ እንደ ሞተባት ሴት ሆኜ አልኖርም፤ ወይም የልጅ ሞት አይደርስብኝም’ ብለሽ በመዝናናት የተቀመጥሽው ቅምጥሊቱ ሆይ! ይህን ስሚ፦ 9 እነዚህ ሁለቱም ነገሮች በቅጽበት በአንድ ቀን በአንቺ ላይ ይደርሳሉ፤ ምንም ያኽል መተትሽ ትልቅ፥ ጥንቈላሽም ብዙ ቢሆን የልጆችና የባል ሞት በአንቺ ላይ በሙላት ይደርሳል። 10 “በክፋትሽ ተዝናናሽ፤ ‘ማንም አያየኝም’ አልሽ፤ ጥበብሽና ዕውቀትሽ አባከኑሽ፤ በልብሽም ‘ማንም እንደኔ ያለ የለም’ አልሽ። 11 በመተትሽ ልታስወግጂ የማትችይው ክፉ ነገር ይመጣብሻል፤ ልትከላከዪ የማትችይው ችግር ይደርስብሻል፤ ምንም ያላሰብሽው ጥፋት በድንገት ያጋጥምሻል። 12 እስኪ ከሆነልሽ ከሕፃንነትሽ ጊዜ ጀምሮ ስትጠቀሚባቸው የኖርሽውን ያፍዝ አደንግዝ ድግምትና የጥንቈላ መተቶችን አስቀምጪ፤ ምንአልባት ጥቂት ይረዳሽ ይሆናል፤ ወይም ጠላቶችሽን ልታስፈራሪባቸው ትችያለሽ፤ 13 የተቀበልሻቸው ምክሮች ሁሉ ያደክሙሻል እንጂ ምንም አይጠቅሙሽም፤ በየወሩ መባቻ ከዋክብትን የሚመለከቱ ኮከብ ቈጣሪዎችሽ ወደፊት ይምጡ፤ በአንቺ ላይ ከሚደርሰውም ችግር ያድኑሽ። 14 “እነሆ፥ እነርሱ እንደ ገለባ እሳት ይበላቸዋል፤ ከነበልባሉ ኀይል ራሳቸውን ሊያድኑ አይችሉም፤ ገለባውም ራስን ለማሞቅ ፍም አይኖረውም። 15 ከወጣትነትሽ ጀምሮ ከአንቺ ጋር ለመጠንቈል ይመላለሱ የነበሩት አስማተኞችም ሁሉ እንደዚሁ በተሳሳተ መንገድ ይባክናሉ፤ ስለዚህ አንቺን ማንም ሊያድንሽ አይችልም።” |