Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 46 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ስለ ባቢሎን ጣዖቶች

1 “ቤልና ኔቦ የተባሉት የሐሰት አማልክት ያጐነብሳሉ፤ ጣዖቶቻቸው በጭነት እንስሶች ላይ ተጭነዋል፤ የተጫኑት ምስሎች ለደካማ እንስሳ ከባዶች ናቸው።

2 የጭነት እንስሶቹ ከክብደቱ የተነሣ ከጭነቱ ጋር አብረው ወደቁ። ጣዖቶቹም ራሳቸውን እንኳ ማዳን ስላልቻሉ ተማርከው ተወሰዱ።

3 “ከማሕፀን ጀምሬ የጠበቅኋችሁና ከልደት ጀምሬ የረዳኋችሁ የያዕቆብ ልጆች የሆናችሁ፥ የእስራኤል ቅሪቶች! አድምጡኝ።

4 አርጅታችሁ ጠጒራችሁ እስከሚሸብትበት ጊዜ ድረስ፥ የምጠብቃችሁ እኔ ነኝ፤ ፈጥሬአችኋለሁ፤ እንከባከባችኋለሁም፤ እረዳችኋለሁ፤ ከክፉ ነገርም እጠብቃችኋለሁ።

5 “ከማን ጋር ታወዳድሩኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር አመሳስላችሁ ታወዳድሩኛላችሁ?

6 አንዳንድ ሰዎች ኰረጆአቸውን ከፍተው ወርቅ እንደ ልባቸው ይመዛሉ፤ ብሩንም በሚዛን ይመዝናሉ፤ ጣዖት አድርጎ እንዲሠራላቸውም አንጥረኛ ይቀጥራሉ፤ ከተሠራም በኋላ እየሰገዱ ያመልኩታል።

7 አንሥተውም በትከሻቸው ይሸከሙታል፤ በአንድ ቦታም ሲያኖሩት በዚያው ይቆማል፤ ካለበት ስፍራም መንቀሳቀስ አይችልም። ማንም ሰው ወደ እርሱ ቢጸልይ መልስ አይሰጠውም፤ ወይም ማንንም ከጥፋት ሊያድን አይችልም።

8 “እናንተ ዐመፀኞች! በአእምሮአችሁ ያዙት፤ በልባችሁም አኑሩት።

9 እኔ ብቻ አምላክ መሆኔንና ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ዕወቁ፤ በቀድሞ ዘመን የተደረጉትን የጥንቱን ነገሮች አስታውሱ፤ እኔ አምላክ ነኝ፤ እኔንም የሚመስል ሌላ የለም።

10 በመጨረሻ የሚሆነውን ነገር ከመጀመሪያው ጀምሬ ተናግሬአለሁ፤ ወደፊት ምን እንደሚሆን ከጥንት ጀምሬ ገልጬአለሁ፤ ዓላማዬ የጸና ይሆናል፤ የምፈቅደውንም አደርጋለሁ።

11 ከወደ ምሥራቅ እንደ ነጣቂ ጭልፊት ያለውን እጠራለሁ፤ እርሱም ዓላማዬን የሚፈጽም፥ ከሩቅ አገር የሚመጣ ሰው ነው፤ የተናገርኩትን አደርጋለሁ፤ ያቀድኩትንም እፈጽማለሁ።

12 “እናንተ ከእውነት የራቃችሁ እልኸኞች አድምጡኝ።

13 ጽድቄን አቀርባለሁ፤ ሩቅም አይደለም፤ ማዳኔ አይዘገይም፤ ኢየሩሳሌምን አድናለሁ፤ ለእስራኤልም ክብሬን አጐናጽፋለሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告