ኢሳይያስ 44 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር ብቸኛ አምላክ መሆኑ 1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የመረጥኳችሁ አገልጋዮቼ የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ሆይ! አድምጡ። 2 በማሕፀን የሠራኋችሁና የምረዳችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ አገልጋዮቼ ስለ ሆናችሁና እኔ ስለ መረጥኳችሁ አትፍሩ። 3 “ለተጠማው ምድር ውሃን እሰጣለሁ፤ በደረቀውም ምድር ጅረቶች እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤ መንፈሴን በልጆችህ ላይ አፈሳለሁ፤ በረከትንም ለልጅ ልጆችህ እሰጣለሁ። 4 እነርሱ ውሃ በደንብ እንደ ጠጣ ሣር፥ በወራጅ ምንጮች አጠገብ እንዳለ የአኻያ ዛፍ ሁልጊዜ የለመለሙ ይሆናሉ። 5 “አንዱ ‘እኔ የእግዚአብሔር ነኝ’ ይላል፤ ሌላው በያዕቆብ ስም ይጠራል፤ ሌላው ደግሞ ‘የእግዚአብሔር ሰው ነኝ’ ብሎ በእጁ ላይ ይነቅሳል፤ እስራኤል በሚለውም ስም ይጠራል።” 6 የሠራዊት አምላክ፥ የእስራኤል ንጉሥና አዳኝ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የመጀመሪያውም የመጨረሻውም እኔ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም። 7 እንደ እኔ ያለ ማነው? እስቲ ካለ ይናገር፤ እስቲ ማስረጃውን በፊቴ ያቅርብ፤ ወደፊት የሚሆነውን አስቀድሞ የተናገረ ማነው? እስቲ ወደፊት የሚሆነውን ይናገር። 8 እናንተ አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ ከጥንት ዘመናት ጀምሮ አስቀድሜ አልነገርኳችሁምን? ወይስ አልገለጽኩላችሁምን? ለዚህም እናንተ ምስክሮቼ ናቸሁ፤ ከእኔ ሌላ አምላክ አለን? ከእኔ ሌላ መጠጊያ አለት የለም፤ ማንም የለም።” በባዕድ አምልኮ ላይ የተደረገ የዘበት አነጋገር 9 ጣዖቶችን የሚሠሩ ሁሉ ከንቱ ናቸው፤ ከፍተኛ ግምት የሚሰጡአቸው ጣዖቶቻቸውም ዋጋቢሶች ናቸው፤ በዚህም ኀፍረት ይደርስባቸዋል። 10 አንድ ሰው ምንም የማይጠቅም ጣዖትን ወይም ምስልን ይሠራል? 11 እነርሱንም የሚያመልኩ ሁሉ ያፍራሉ፤ ጣዖትን የሚሠሩ ሰዎች እንጂ ሌላ አይደለም፤ ሁሉም ይሰብሰቡና በፊቴ ይቁሙ፤ ሁሉም በፍርሃት ይዋጣሉ፤ ያፍራሉም። 12 አንጥረኛ ጣዖትን ለመሥራት ብረትን ወስዶ በእሳት ያቀልጠዋል። ለብረቱም ቅርጽ ለመስጠት በብርቱ ክንዱ በመዶሻ ይቀጠቅጠዋል፤ ይህንንም በሚሠራበት ጊዜ ይራባል፥ ይጠማል፥ ይደክማልም። 13 አናጢ በእንጨቱ ላይ መስመርን ያሰምራል፤ ንድፍም ይነድፋል፤ በመላጊያ ያለሰልሰዋል፤ በማስተካከያ መሣሪያም ትክክልነቱን ያረጋግጣል፤ ውበት ያለው የሰው ቅርጽ እንዲኖረው ያደርጋል። ከዚያም በጣዖት ቤት ያኖረዋል። 14 ይህን ለማድረግ የሊባኖስ ዛፍ ወይም ዝግባ ዛፍ ወይም ዋርካ ከጫካው ይመርጣል፤ አለበለዚያም በአናጢው ተተክሎ የዝናብ ውሃ እየጠጣ የሚያድገውን የኮምበል ዛፍ ይተክላል። 15 ሰው ከአንድ ዛፍ ግማሹን ለማገዶ፥ ግማሹንም ጣዖት ለመሥራት ይጠቀምበታል፤ ግማሹን እሳት አንድዶ ለመሞቅና እንጀራ ለመጋገር ይጠቀምበታል፤ በሌላው ጒማጅ ጣዖት ሠርቶ በፊቱ እየሰገደ ያመልከዋል። 16 ግማሹን እሳት አንድዶ ምግቡን ያዘጋጅበታል፤ ሥጋም ጠብሶ እስከሚጠግብ ይመገባል፤ ከሞቀውም በኋላ “ግሩም እሳት ነው! እንዴት ይሞቃል!” ይላል። 17 የቀረውንም ጒማጅ ጣዖት አድርጎ ይሠራና በፊቱ ተደፍቶ በመስገድ ያመልከዋል፤ “አንተ አምላኬ ነህ፤ አድነኝ!” እያለ ወደ እርሱ ይጸልያል። 18 እንደዚህ ያሉት ሰዎች ዐይኖቻቸው ስለ ተሸፈኑ ማየት አይችሉም። 19 “የዚህን እንጨት ግማሹን አነደድኩት፤ በፍሙም ዳቦ ጋገርኩበት፤ ሥጋም ጠብሼበት በላሁ፤ አሁን እንግዲህ ቀሪውን ቊራጭ እንጨት ለጣዖት ላውለውን? በአንድ ቊራጭ እንጨት ፊት ወድቄ ልስገድን?” ብሎ የሚያስብ ዕውቀት ወይም ማስተዋል ያለው አንድም ሰው የለም። 20 ተቃጥሎ ዐመድ የሚሆነውን እንጨት እስከ ማምለክ ድረስ ሰው እንዴት ሞኝ ይሆናል? የሞኝነት አስተሳሰቡ አሳስቶታል፤ ራሱን ማዳን አይችልም፤ ወይም “ይህ በቀኝ እጄ ያለው ነገር ጣዖት እንጂ አምላክ አይደለም።” ብሎ መናገር አይችልም። የእግዚአብሔር ፈጣሪነትና አዳኝነት 21 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እስራኤል ሆይ! ይህን አስታውስ፤ እኔ ፈጠርኩህ፤ አንተም አገልጋዬ መሆንህን አትርሳ፤ እኔም አልረሳህም። 22 በደልህን እንደ ደመና ኃጢአትህን እንደ ማለዳ ጭጋግ አስወግጄአለሁ፤ ስለ አዳንኩህ ወደ እኔ ተመለስ።” 23 ሰማያት ሆይ! እግዚአብሔር ሕዝቡን እስራኤልን በማዳን ክብሩን ገልጦአልና በደስታ ዘምሩ፤ ምድርም ከታች እልል በዪ፤ ተራራዎች፥ ጫካዎችና በውስጣቸው የምትገኙ ዛፎች ሁሉ የደስታ ድምፅ እያሰማችሁ ፈንድቁ። 24 በእናትህ ማሕፀን የፈጠረህ አዳኝህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሁሉን ነገር የፈጠርኩ፥ ሰማያትን ብቻዬን የዘረጋሁ፥ ምድርንም ብቻዬን ያነጠፍኩ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 25 የሐሰተኞች ነቢያትን ምልክቶችና፥ የሟርተኞችን ጥንቈላ ከንቱ አደርጋቸዋለሁ። የጥበበኞችን ዕውቀት እገለብጣለሁ፤ ዕውቀታቸውንም ወደ ሞኝነት እለውጠዋለሁ፤ 26 የአገልጋዮቼን መልእክት አጸናለሁ፤ የነቢያቴንም ትንቢት እንዲፈጸም አደርጋለሁ፤፥ እነርሱም ኢየሩሳሌም፦ ‘የብዙ ሕዝብ መኖሪያ ትሆናለች፤ የይሁዳ ከተሞችም እንደገና ይሠራሉ፤ ፍርስራሾቻቸውም ይታደሳሉ’ ይላሉ። 27 ውቅያኖሱን ‘እኔ ወንዞችህን ስለማደርቅ አንተ ድረቅ’ እለዋለሁ፤ 28 ቂሮስን ‘የመንጋዬ እረኛ ነህ፤ ዕቅዴን ሁሉ ትፈጽማለህ’ እለዋለሁ፤ ኢየሩሳሌምን ‘አንቺ እንደገና ትገነቢአለሽ’ ቤተ መቅደሱን፥ ‘መሠረትህ ይጣላል’ እላቸዋለሁ።” |