Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 43 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመታደግ የሰጠው ተስፋ

1 የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ሆይ! የፈጠራችሁ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የታደግኋችሁ ስለ ሆነ አትፍሩ፤ እናንተ የእኔ ናችሁ፤ በስማችሁም ጠርቼአችኋለሁ።

2 በውሃ ውስጥ በምታልፉበት ጊዜ እኔ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ፤ በወንዞች መካከል በምታልፉበት ጊዜ አያሰጥሙአችሁም፤ በእሳትም ውስጥ በምታልፉበት ጊዜ አያቃጥላችሁም፤ ነበልባሉም ዐመድ አያደርጋችሁም።

3 እኔ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር አምላካችሁና አዳኛችሁ ነኝ፤ እናንተን ለመታደግ ግብጽን፥ ኢትዮጵያውያንንና ሳባን እሰጣለሁ።

4 እናንተ በእኔ ፊት የተወደዳችሁ ናችሁ፤ ስለምወዳችሁ ሕይወታችሁን ለማዳን ሕዝቦችንና መንግሥታችን አሳልፌ እሰጣለሁ።

5 እኔ ከእናንተ ጋር ስለ ሆንኩ አትፍሩ፤ ከምሥራቅም ከምዕራብም እናንተንና ልጆቻችሁን ሰብስቤ አመጣለሁ።

6 “ወንዶች ልጆቼ ከሩቅ አገር እንዲመጡ በሰሜን በኩል ያሉትን አገሮች ተዉአቸው፥ በደቡብ በኩል ያሉትን አገሮች ‘አትያዙአቸውም’ ብዬ አዛለሁ።

7 እነርሱ በስሜ የተጠሩና ለክብሬ የፈጠርኳቸው በእጄም የአበጀኋቸውና የሠራኋቸው ሕዝቤ ናቸው።”


እስራኤል የእግዚአብሔር ምስክር መሆኑ

8 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ዐይን እያላቸው የማያዩ ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ፥ ሕዝቤን በአንድነት ሰብስቡ!

9 ሕዝቦች ሁሉ በአንድነት ይሰብሰቡ፤ ከእነርሱ መካከል የአሁንና የቀድሞዎቹን ነገሮች አስቀድሞ የተናገረና የገለጠ ማነው? እውነተኛነታቸውን ለማረጋገጥ ምስክሮቻቸውን ያምጡ። እነርሱም ሰምተው እውነት ነው ይበሉ።

10 “እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ተረድታችሁ ታውቁኝና ታምኑብኝ ዘንድ የመረጥኳችሁ አገልጋዮቼና ምስክሮቼ እናንተ ናችሁ። በእርግጥ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ ከእዚህ በፊት አልነበረም፤ ወደ ፊትም አይኖርም።

11 “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም ሌላ የሚያድን የለም

12 እኔ ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድሜ ተናግሬአለሁ፤ እናንተን ያዳንኩ እኔ ነኝ፤ ከባዕዳን አማልክት አንድ እንኳ ይህን አላደረገም፤ ለዚህ ሁሉ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ።

13 እኔ ከጥንት ጀምሮ አምላክ ነኝ፤ ከእጄ ማንም ማንንም አያድንም፤ እኔ ያደረግኹትን መለወጥ የሚችል የለም።”


ከባቢሎን ማምለጥ

14 አዳኛችሁ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ስለ እናንተ በባቢሎን ላይ የሚዘምት ሠራዊት እልካለሁ፤ የከተማዋን ቅጽር በሮች እሰባብራለሁ፤ የባቢሎናውያንም ፉከራ ወደ ለቅሶ ይለወጣል።

15 እኔ እግዚአብሔር የእናንተ ቅዱስ አምላክ ነኝ፤ እስራኤል ሆይ! እኔ ፈጠርኳችሁ፤ ንጉሣችሁም እኔ ነኝ።”

16 እግዚአብሔር በባሕር መካከል መንገድን ሠራ፤ በውሃ መካከል መተላለፊያን አበጀ፥

17 ሠረገሎችንና ፈረሶችን፥ የጦር ሠራዊትንና ጀግኖችን ወደ ጥፋታቸው መራቸው፤ እነርሱ ወደቁ፤ ዳግመኛም አይነሡም፤ እፍ ሲሉት እንደሚጠፋ ጧፍም ሆኑ።

18 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ያለፉትን ድርጊቶች አታስታውሱ፤ ከዚህ በፊት የሆነውንም ነገር አታሰላስሉ።

19 ይልቅስ የማደርገውን አዲስ ነገር ተመልከቱ፤ እርሱም በመፈጸም ላይ ስለ ሆነ ልታዩት ትችላላችሁ፤ በበረሓ መንገድን አወጣለሁ፤ በምድረ በዳም ወንዞችን አፈልቃለሁ።

20 ለተመረጡት ሕዝቤ ውሃን ለመስጠት ወንዞች በበረሓ ጅረቶች በምድረ በዳ እንዲፈስሱ ባደረግሁ ጊዜ የምድር አራዊት እንኳ ሳይቀሩ ያከብሩኛል፤ ቀበሮዎችና ሰጎኖችም ያመሰግኑኛል።

21 እነርሱም ለራሴ የሠራኋቸው ሕዝቦች ስለ ሆኑ እኔን ያመሰግናሉ።”


የእስራኤል ኃጢአት

22 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል! “የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ሆይ፥ እናንተ ስሜን መጥራት ትታችኋል፤ ልታገለግሉኝም አልፈለጋችሁም።

23 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆኑ በጎቻችሁን አላቀረባችሁልኝም፤ በመሥዋዕታችሁም አላከበራችሁኝም፤ እኔም መባ እንድታቀርቡልኝ በመጠየቅ ሸክም አልሆንኩባችሁም፤ ‘ዕጣን አቅርቡልኝም’ ብዬ አላሰለቸኋችሁም።።

24 በገንዘባችሁ መልካም መዓዛ ያለው ዕጣን አልገዛችሁልኝም፤ ወይም በስብ መሥዋዕታችሁ አላረካችሁኝም፤ ነገር ግን በኃጢአታችሁ ብዛት ሸክም ሆናችሁብኝ። በበደላችሁም ብዛት አሰለቻችሁኝ።

25 ይህም ሁሉ ሆኖ ኃጢአታችሁን ይቅር የምል አምላክ እኔ ነኝ፤ ይህንንም የማደርገው ስለ እናንተ ሳይሆን ስለ እኔነቴ ነው፤ ስለዚህ ኃጢአታችሁን አልቈጥርባችሁም።

26 “አስታውሱኝ፤ ጉዳያችሁን አቅርባችሁ ትክክለኛነታችሁን አስመስክሩ።

27 የመጀመሪያ አባታችሁ ኃጢአት ሠራ፤ አስተማሪዎቻችሁም በደል በመፈጸም እኔን አሳዘኑ።

28 ስለዚህ የቤተ መቅደስን ሹማምንት ርኲሰት ገለጥኩ፤ የያዕቆብም ልጆች እስራኤላውያን እንዲዋረዱና ፈጽመውም እንዲጠፉ አደረግሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告