Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 39 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ከባቢሎን የመጡ መልእክተኞች
( 2ነገ. 20፥12-19 )

1 በዚያን ዘመን የባቢሎን ንጉሥ የባላዳን ልጅ መሮዳክ ባላዳን ንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ መዳኑን ሰማ፤ ስለዚህም ከገጸ በረከት ጋር ደብዳቤ ላከለት።

2 ሕዝቅያስም መልእክተኞቹን በደስታ ተቀበላቸው፤ በቤተ መንግሥቱም የዕቃ ግምጃ ቤት ያለውን ሀብት በሙሉ ብሩንና ወርቁን፥ ቅመማ ቅመሙንና፥ ሽቶውን፥ የጦር መሣሪያውንና በዕቃ ቤት ያለውን ንብረት ሁሉ አሳያቸው፤ በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤትም ሆነ በመንግሥቱ በማንኛውም ስፍራ ካለው ሀብት ሁሉ ሕዝቅያስ ያላሳያቸው ምንም ነገር አልነበረም።

3 በዚያም ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሄዶ “እነዚህ ሰዎች ከወዴት መጡ? ምንስ ነገሩህ?” ብሎ ጠየቀው። ሕዝቅያስም “እነርሱ የመጡት ባቢሎን ከሚባል ከሩቅ አገር ነው” ሲል መለሰለት።

4 ኢሳይያስም “በቤተ መንግሥቱ ምን አዩ?” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “ሁሉን ነገር አይተዋል፤ በግምጃ ቤት ካለው ሀብት ሁሉ ለእነርሱ ያላሳየኋቸው ምንም ነገር የለም” አለው።

5 ኢሳይያስም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦

6 የቀድሞ አባቶች እስከዚህች ቀን ያከማቹት በቤተ መንግሥትህ ያለው ሀብት ሁሉ ተጠራርጎ ወደ ባቢሎን የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ ምንም ነገር አይቀርልህም።

7 ከአንተም ዘር አንዳንዶቹ ወደ ባቢሎን ተማርከው በመሄድ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ጃንደረባ ሆነው እንዲያገለግሉ ይደረጋል።”

8 ንጉሥ ሕዝቅያስ በተለይ በእርሱ ዘመን፥ በሰላም የመኖር ዋስትና እንዳለ ስለ ተረዳ “ከእግዚአብሔር ተልከህ የነገርከኝ ቃል መልካም ነው” አለ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告