ኢሳይያስ 38 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ ስለ መዳኑ ( 2ነገ. 20፥1-11 ፤ 2ዜ.መ. 32፥24-26 ) 1 በዚያን ዘመን ንጉሥ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ለመሞት ተቃርቦ ነበር፤ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ሊጐበኘው ወደ እርሱ ሄዶ “እግዚአብሔር ‘ከሕመምህ አትድንም፤ መሞትህም ስለማይቀር ቤትህን አዘጋጅ’ ብሎሃል” ሲል ነገረው። 2 ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፦ 3 “አምላክ ሆይ! በታማኝነትና በሙሉ ልብ እንዳገለገልኩህ፥ አንተ የምትደሰትበትንም ነገር እንዳደረግሁ አስታውስ፤” ምርር ብሎም አለቀሰ። 4 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ኢሳይያስን እንዲህ አለው፦ 5 “ወደ ሕዝቅያስ ሄደህ እንዲህ በለው፤ ‘እነሆ፥ የቀድሞ አባትህ የዳዊት አምላክ እኔ እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰምቼአለሁ፤ እንባህንም አይቼአለሁ፤ ስለዚህም በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት ጨምሬልሃለሁ፤ 6 አንተንና ይህችን የኢየሩሳሌምን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ከተማይቱንም በመከላከል እጠብቃለሁ።’ ” 7 ኢሳይያስም እንዲህ ሲል መለሰለት፥ “እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል የሚፈጽም ስለ መሆኑ የሚሰጥህ ምልክት ይህ ነው፤ 8 ንጉሥ አካዝ ባሠራው የመወጣጫ ደረጃ ላይ የሚያርፈውን ጥላ እግዚአብሔር እንደገና ዐሥር ደረጃዎችን አልፎ ወደ ኋላ እንዲመለስ ያደርገዋል።” ጥላውም ዐሥር ደረጃዎችን አልፎ ወደ ኋላ ተመለሰ። 9 ሕዝቅያስም ከሕመሙ እንደ ተፈወሰ የሚከተለውን የምስጋና መዝሙር ጻፈ፦ 10 እኔ ገና በመካከለኛ ዕድሜዬ ሳለሁ የመኖር ዕድል ተነፍጎኝ ወደ ሙታን ዓለም የምወርድ መስሎኝ ነበር። 11 ሕያዋን በሚኖሩበት በዚህ ዓለም እግዚአብሔርን ወይም ከሕያው ፍጡር ሁሉ መካከል ሰውን ዳግመኛ አላይም ብዬ ነበር። 12 ሕይወቴ በድንገት እንደ እረኛ ድንኳን የተነቀለና የተጠቀለለ፥ ተሠርቶም ሳያልቅ ከሸማኔው መጠቅለያ እንደ ተቈረጠ ልብስ ሆነ ብዬ አስቤ ነበር፤ እግዚአብሔር ሕይወቴን በአጭር የቀጫት መስሎኝ ነበር። 13 እስከ ንጋት ድረስ ስጮኽ ዐድራለሁ፤ እንደ አንበሳም አጥንቶቼን ሁሉ ሰባበርክ፤ ሌሊትና ቀንም ለሥቃይ አሳልፈህ ሰጠኸኝ። 14 እንደ ሽመላ እጮኽ ነበር፤ እንደ ርግብ የሐዘን ድምፅ አሰማ ነበር፤ ወደ ሰማይም አሻቅቤ ከመመልከቴ የተነሣ፥ ዐይኖቼ በጣም ደክመው ነበር። ጌታ ሆይ! እባክህን ከዚህ ሁሉ መከራ አድነኝ! 15 ይህን ሁሉ ያደረገው እግዚአብሔር ራሱ ስለ ሆነ፥ ምን ማለት እችላለሁ? ከምሬቴ የተነሣ እንቅልፌ ሁሉ ጠፍቶ ነበር። 16 ነፍሴ ካንተ ሕይወትን ታገኛለች፤ ለመንፈሴ ዕረፍትን ስጣት፤ ጤንነቴን እንደ ነበረ አድርግልኝ፥ ሕይወትንም ስጠኝ። 17 ችግር የደረሰብኝ በእርግጥ ለደኅንነቴ ነው፤ ከአደጋም ሁሉ ሕይወቴን ታድናለህ፤ ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር ትላለህ። 18 ከሙታን ዓለም ሊያመሰግንህ የሚችል አንድ እንኳ የለም፤ ሙታንም ሊያመሰግኑህ አይችሉም፤ ወደ መቃብር የወረዱትም ታማኝነትህን ተስፋ አያደርጉም። 19 እኔ አሁን እንደማመሰግንህ ሊያመሰግኑህ የሚችሉት ሕያዋን ብቻ ናቸው፤ አባቶች ለልጆቻቸው የአንተን ታማኝነት ይናገራሉ። 20 እግዚአብሔር ያድነኛል፤ ስለዚህ እኛ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ አውታር ባለው የሙዚቃ መሣሪያ የምሥጋና መዝሙር በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዘምራለን። 21 ከዚህ በኋላ ኢሳይያስ የበለስ ቅጠሎችን ጥፍጥፍ በእባጩ ላይ ቢያደርጉ ይፈወሳል ብሎአቸው ነበር። 22 ንጉሥ ሕዝቅያስም “ድኜ ወደ ቤተ መቅደስ ለመሄድ እንደምችል የማውቀው በምን ምልክት ነው?” ሲል ኢሳይያስን ጠየቀ። |