Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 37 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ንጉሥ ሕዝቅያስ የኢሳይያስን ምክር መጠየቁ
( 2ነገ. 19፥1-7 )

1 ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደ።

2 የቤተ መንግሥቱን አዛዥ ኤልያቄምን፥ የቤተ መንግሥቱን ዋና ጸሐፊ ሼብናንና ከካህናት መካከል ታዋቂዎች የሆኑትን ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ላከ፤ እነርሱም ማቅ ለብሰው ነበር።

3 እነርሱም ከሕዝቅያስ ተቀብለው ለኢሳይያስ የነገሩት መልእክት ይህ ነበር፦ “ዛሬ የታላቅ መከራ ቀን ነው፤ የሚያሳፍር ቅጣትና ውርደት እየደረሰብን ነው፤ የምትወልድበት ጊዜ ደርሶ ለማማጥ አቅም እንዳነሣት ሴት ሆነናል፤

4 የአሦር ንጉሥ ሕያው እግዚአብሔርን እንዲሰድብለት ከፍተኛ ባለሥልጣኑን ልኮአል፤ አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ስድብ ሰምቶ ተሳዳቢውን ይቀጣ ይሆናል፤ ስለዚህ ከሕዝባችን መካከል በሕይወት ስለሚተርፉት እባክህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ።”

5 ኢሳይያስም ንጉሥ ሕዝቅያስ የላከውን መልእክት ሰምቶ፥

6 ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ላከ፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች እኔን የሰደቡበትን የስድብ ቃል በመስማትህ አትፍራ።’

7 በሀገሩ ስላለ ጉዳይ በሹክሹክታ ወሬ እንዲሸበርና ወደ ሀገሩ ተመልሶ በሰይፍ እንዲገደል አደርገዋለሁ።”


አሦራውያን ሌላ የዛቻ መልእክት መላካቸው
( 2ነገ. 19፥8-19 )

8 የአሦራውያን ባለ ሥልጣን ንጉሡ ላኪሸን ለቆ በአቅራቢያ ወዳለችው ወደ ሊብና ከተማ በመሄድ እዚያ በመዋጋት ላይ መሆኑን ሰማ፤ ስለዚህ ወደዚያ ሄደ።

9 በኢትዮጵያ ንጉሥ በቲርሃቃ የሚመራ የግብጽ ሠራዊት እነርሱን ለመውጋት በመገሥገሥ ላይ መሆኑን አሦራውያን ሰሙ፤ የአሦር ንጉሥ ይህን በሰማ ጊዜ ወደ ሕዝቅያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ በመልእክተኛ እጅ ላከ፦

10 “የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሆይ! የምትታመንበት አምላክ ‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትወድቅም!’ ብሎ ተስፋ በመስጠት አያታልህ።

11 የአሦር ነገሥታት አንድን አገር ለማጥፋት በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ እንዴት እንደሚያወድሙአት ሰምተሃል፤ ታዲያ፥ አንተስ ከዚህ የምታመልጥ ይመስልሃልን?

12 የቀድሞ አባቶቼ የጎዛንን፥ የካራንና የሬጼፍን ከተሞች አጥፍተዋል፤ በተላሳር ይኖሩ የነበሩትን የዔደንን ሕዝብ ገድለዋል፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ከአማልክታቸው አንዳቸው እንኳ ሊያድኑአቸው ችለዋልን?

13 የሐማት፥ የአርፋድ፥ የሰፋርዋይም የሄናዕና የዒዋ ከተሞች ነገሥታት አሁን ወዴት አሉ?”


የሕዝቅያስ ጸሎት

14 ንጉሥ ሕዝቅያስ ደብዳቤውን ከመልእክተኞቹ እጅ ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ ቤተ መቅደስም ወስዶ ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት በማቅረብ፥

15 እንዲህ ሲል ጸለየ

16 “የሠራዊት ጌታ የእስራኤል አምላክ ሆይ! በኪሩቤል ላይ ዙፋን የዘረጋ አምላክ አንተ ብቻ ነህ፤ የዓለምም መንግሥታት ሁሉ አምላክ አንተ ነህ፤ ሰማይና ምድርን የፈጠርክ አንተ ነህ።

17 አምላክ ሆይ! ሰናክሬም! እንዴት አድርጎ አንተን ሕያው አምላክን እንደ ዘለፈ ተመልከት።

18 አምላክ ሆይ! የአሦር ነገሥታት ብዙ መንግሥታትን ማጥፋታቸውንና ምድራቸውንም መደምሰሳቸውን ሰምተናል።

19 እንጨቱን በመጥረብ፥ ድንጋዩን በማለዘብ በሰው እጅ የተሠሩ ከንቱ የሆኑ አማልክታቸውን በእሳት አቃጥለው አጥፍተዋል።

20 እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ! አንተ ብቻ አምላክ መሆንህን የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ያውቁ ዘንድ አሁን ከአሦራውያን እጅ በመታደግ አድነን።”


ኢሳይያስ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ያስተላለፈው መልእክት
( 2ነገ. 19፥2-37 )

21 ከዚህ በኋላ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ዛቻ ያቀረብከውን ጸሎት ሰምቼአለሁ፤’

22 ስለ እርሱም እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይህ ነው፥ ‘ሰናክሬም ሆይ! የኢየሩሳሌም ሕዝብ አንተን በመናቅ ያፌዙብሃል፤ በምትሸሽበትም ጊዜ ከበስተኋላህ ሆነው ራሳቸውን ይነቀንቁብሃል።

23 ዐይንህን በትዕቢት አቅንተህ፥ ድምፅህን ከፍ አድርገህ በመጮኽ የተዳፈርከውና የተሳደብከው ማንን ይመስልሃል? የእስራኤልን ቅዱስ አይደለምን?’

24 አገልጋዮችህን ልከህ በጌታ ላይ የስድብ ቃል በመናገር፦ ‘በሠረገሎቼ ብርታት ከፍተኛ የሆኑ የሊባኖስ ተራራዎችን ይዤአለሁ፤ ረጃጅም የሆኑትን የሊባኖስ ዛፎችና የተዋቡ የዝግባ ዛፎችን ቈርጬአለሁ፤ በከፍተኛ ስፍራዎች ላይ ጥቅጥቅ ወዳሉት ደኖች አልፌአለሁ፤

25 በባዕዳን አገሮች ጒድጓዶችን ቆፍሬ ውሃ ጠጥቻለሁ፤ የብዙ ሠራዊቴ እግር የግብጽን ወንዞች አድርቋል’ ብለህ ተመክተሃል።

26 “ከብዙ ጊዜ በፊት ይህን ሁሉ የወሰንኩት እኔ ራሴ መሆኔን አልሰማህምን? ዕቅዱን አውጥቼ አሁን ለፍጻሜ ያደረስኩት እኔ ነኝ፤ የተመሸጉ ከተሞችን የፍርስራሽ ክምር እንድታደርጋቸው ኀይልን የሰጠሁህ እኔ ነኝ።

27 የሕዝቦቻቸው ኀይል ተዳክሞአል፤ እነርሱም ተስፋ ቈርጠው ዐፍረዋል፤ እንደ ሜዳ አበባ፥ እንደ ለጋ ሣር፥ በጣራ ላይ እንደሚበቅልና ፈጥኖ እንደሚጠወልግ ጓሳ ናቸው።

28 “እኔ ስለ አንተ ሁሉን ነገር ዐውቃለሁ፤ ምን እንደምታደርግና ወዴት እንደምትሄድ እመለከታለሁ፤ በእኔ ላይ በቊጣ መነሣሣትህንም ተረድቼአለሁ።

29 በእኔ ላይ ስለ መቈጣትህና ስለ ልብህ ትዕቢት ሁሉ ሰምቼአለሁ፤ ስለዚህ አሁን በአፍንጫህ ስናጋ፥ በአፍህም ልጓም አግብቼ በመጣህበት መንገድ እመልስሃለሁ።”

30 ከዚህ በኋላ ኢሳይያስ ንጉሥ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፦ “ይህ ሁሉ እንደሚፈጸም ምልክቱ ይህ ነው፦ በአሁኑና በሚቀጥለው ዓመት ሳይዘሩት የበቀለውንና የገቦውን እህል ትበላላችሁ፤ በሦስተኛው ዓመት ግን የራሳችሁን እህል ዘርታችሁ ታመርታላችሁ፤ ወይንም ተክላችሁ ፍሬውን ትበላላችሁ።

31 በይሁዳ ከጥፋት የተረፉት ሁሉ ወደ መሬት ሥር ሰዶ እንደሚያድግና እንደሚያፈራ ተክል ይሆናሉ።

32 ይህ ሁሉ እንዲፈጸም የሠራዊት አምላክ ቅናት ስለ ወሰነ ከኢየሩሳሌምና ከጽዮን ኰረብታ ከጥፋት የሚተርፉ ይኖራሉ።

33 “ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ አሦራውያን ንጉሥ የተናገረውም ቃል ይህ ነው፤ ‘ሰናክሬም ወደዚህች ከተማ ፈጽሞ አይገባባትም፤ አንድ ፍላጻ እንኳ አይወረውርባትም፤ ጋሻ ያነገበ ወታደርም ወደ እርስዋ አይቀርብም፤ በዐፈር ቊልልም አትከበብም።

34 ስለዚህም እርሱ ወደዚህች ከተማ ሳይገባ በመጣበት መንገድ ተመልሶ ይሄዳል፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

35 ስለ ራሴ ክብርና ለአገልጋዬ ለዳዊት ስለ ሰጠሁት የተስፋ ቃል ይህችን ከተማ እኔ ራሴ በመከላከል አድናታለሁ።’ ”

36 በዚያው ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወደ አሦራውያን ሰፈር አልፎ መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ወታደሮችን ገደለ፤ በማግስቱ በማለዳ ሰዎች በሚነቁበት ጊዜ ሁሉም ሞተው ተገኙ።

37 ከዚህ በኋላ የአሦራውያን ንጉሥ ሰናክሬም ወደኋላው በማፈግፈግ ወደ ነነዌ ተመልሶ በዚያ ኖረ።

38 ከዕለታት በአንዱ ቀን ኒሰሮክ በሚል ስም በሚጠራው ጣዖት ቤተ መቅደስ ውስጥ በስግደት ላይ እንዳለ ከልጆቹ ሁለቱ በተለይ አድራሜሌክና ሣሬጼር ተብለው የሚጠሩት በሰይፍ ገደሉት፤ እነርሱም ወደ አራራት አምልጠው ሄዱ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ከልጆቹ አንዱ አስራዶን የተባለው ነገሠ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告