ኢሳይያስ 36 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበኢየሩሳሌም ላይ የሰናክሬም ዛቻ ( 2ነገ. 18፥13-27 ፤ 2ዜ.መ. 32፥1-19 ) 1 ሕዝቅያስ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት፥ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ላይ አደጋ ጥሎ ያዛቸው። 2 ንጉሥ ሕዝቅያስ እጁን እንዲሰጥ ይጠይቀው ዘንድ የአሦር ንጉሥ የጦር አዛዡን፥ ከብዙ ሠራዊት ጋር ከላኪሽ ወደ ኢየሩሳሌም ላከው፤ እርሱም ሄዶ የላይኛው ኲሬ ውሃ በሚተላለፍበት ቦይ አካባቢ በሚገኘው በልብስ አጣቢው ቦታ አጠገብ ቆመ። 3 እርሱንም ለመገናኘት የቤተ መንግሥቱ አዛዥ የነበረው የሒልቅያ ልጅ ኤልያቄም፥ ጸሐፊ የነበረው ሺብና፥ መዝጋቢ የነበረው የአሳፍ ልጅ ዮአሕ ወጡ። 4 የአሦር ባለ ሥልጣን የነበረው ራፋስ ቂስ እንዲህ አላቸው፦ “ለንጉሥ ሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ‘እነሆ፥ የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፦ ለመሆኑ ይህን ያኽል ልበ ሙሉ የሆንከው በማን ተማምነህ ነው? 5 ከንቱ ቃላት የጦርነት ስልትና ኀይል ይሆናል ብለህ ታስባለህን? ኧረ ለመሆኑ በእኔ ላይ ያመፅከው በማን ተማምነህ ነው? 6 ምንአልባት ግብጽ ትረዳኛለች ብለህ ተስፋ አድርገህ ይሆናል፤ ነገር ግን በእርስዋ መታመን በሸምበቆ የመደገፍ ያኽል መሆኑን ዕወቀው፤ ተሰንጥሮ እጅህን ከሚወጋው በቀር ሸምበቆ ለምንም አይጠቅምህም፤ በግብጽ ንጉሥ የሚተማመንም የሚገጥመው ዕድል ይህንኑ የመሰለ ነው።’ ” 7 የአሦራውያን ባለ ሥልጣን ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ ‘እኔ የምታመነው በአምላኬ በእግዚአብሔር ነው’ ትል ይሆናል፤ ታዲያ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በዚህ በአንድ መሠዊያ ብቻ እንዲያመልኩ ፈልገህ የእግዚአብሔርን መሠዊያዎችና የማምለኪያ ስፍራዎች ያፈራረስክ አንተ ሕዝቅያስ አይደለህምን? 8 ስለዚህ በአሦር ንጉሠ ነገሥት ስም ሆኜ የሚበጅህን ነገር እነግርሃለሁ፤ ተቀምጠውባቸው ለመጋለብ የሚደፍሩ ሰዎች ካሉህ ሁለት ሺህ ፈረሶችን እሰጥሃለሁ። 9 አንተ ከአሦራውያን ባለሥልጣኖች የመጨረሻውን ዝቅተኛ መኰንን እንኳ ለመቋቋም የምትችል አይደለህም፤ ይህም ሆኖ ግብጻውያን ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን ይልኩልኛል ብለህ ተስፋ ታደርጋለህ። 10 እኔስ ብሆን ይህንን አገር ለመውረርና ለማጥፋት የቻልኩት ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመስልሃልን? እንዲያውም በአገሪቱ ላይ አደጋ ጥዬ እንዳጠፋት ያዘዘኝ እግዚአብሔር ራሱ ነው።” 11 ከዚህ በኋላ ኤልያቄም፥ ሼብናና ዮአሕ የአሦራውያኑን ባለ ሥልጣን “እኛ ትርጒሙን ስለምናውቅ በሶርያ ቋንቋ እንድትነግረን እንለምንሃለን፤ በቅጽር ላይ ያሉት ሕዝብ ሁሉ በሚሰሙት በዕብራይስጥ ቋንቋ አትንገረን” አሉት። 12 የአሦራውያን ባለሥልጣንም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታዬ የአሦር ንጉሥ ይህን ሁሉ ለእናንተና ለንጉሣችሁ ብቻ እንድናገር የላከኝ መሰላችሁን? ከቶ አይደለም፤ ልክ እንደ እናንተ ዐይነ ምድራቸውን መብላትና ሽንታቸውን መጠጣት ያለባቸው ሕዝቡም ጭምር ስለ ሆኑ እኔ የምናገረውን በቅጽሩ ላይ ያሉት ሕዝቡ ሁሉ እንዲሰሙት ነው።” 13 ስለዚህ የአሦር ባለ ሥልጣን ከተቀመጠበት ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ እያለ መናገር ጀመረ፦ “የታላቁን የአሦር ንጉሥ ቃል ስሙ! 14 በሕዝቅያስ አትታለሉ፤ እርሱ ሊያድናችሁ ከቶ አይችልም፤ 15 ሕዝቅያስ ‘በእግዚአብሔር ተማመኑ፤ እርሱ ያድነናል፤ ከተማችንም በአሦራውያን ሠራዊት እጅ እንዳትገባ ይከላከልልናል’ እያለ የሚያግባባችሁን አትስሙት። 16 ሕዝቅያስ የሚላችሁን አታዳምጡ! የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፦ ወደ እኔ ኑና ከእኔ ጋር ተስማምታችሁ ኑሩ፤ ይህን ብታደርጉ ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ የወይን ተክሎቻችሁን ዘለላ የበለስ ዛፎቻችሁን ፍሬ ትበላላችሁ፤ ከጒድጓዶቻችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ። 17 ይህም የሚሆነው ንጉሡ የእናንተን አገር ወደምትመስል ምድር ወስዶ እስከሚያሰፍራችሁ ድረስ ነው፤ በዚያችም ምድር የወይን ጠጅ የሚገኝባቸው የወይን ተክል ቦታዎችና በቂ የእንጀራ እህል የሚመረትባቸው እርሻዎች አሉ፤ 18 ስለዚህ ሕዝቅያስ ‘እግዚአብሔር ታደጋችኋል!’ እያለ በማሳሳት አያሞኛችሁ፤ ለመሆኑ ከሌሎች ሕዝቦች አማልክት መካከል አንድ እንኳ ከአሦር ንጉሥ እጅ አገሩን ለማዳን የቻለ ይገኛልን? 19 ታዲያ ይህ ከሆነ የሀማትና የአርፋድ አማልክት የት አሉ? የሰፋርዋይም አማልክትስ የት ደረሱ? ለመሆኑ ከእነርሱ አንዱ እንኳ ሰማርያን ከእጄ ሊያድን ችሎአልን? 20 የእነዚህ ሁሉ አገሮች አማልክት ከእኔ እጅ አገራቸውን ለማዳን የቻሉበት ጊዜ አለን? ታዲያ እናንተ ‘እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ያድናታል’ ብላችሁ የምታስቡት እንዴት ነው?” 21 ሕዝቡም ቀደም ሲል ንጉሥ ሕዝቅያስ ባዘዛቸው መሠረት አንዲት ቃል ሳይናገሩ ዝም አሉ። 22 ከዚህ በኋላ የቤተ መንግሥት አዛዥ የነበረው የሕልቂያ ልጅ ኤልያቄም፥ ጸሐፊው ሼብናና የታሪክ መዝጋቢ የነበረውም የአሳፍ ልጅ ዮአሕ በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስም ቀርበው የአሦርያውያን ባለሥልጣን የተናገረውን ሁሉ አስረዱ። |