Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 35 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የቅድስና አገር

1 በረሓውና ደረቁ ምድር ደስ ይለዋል፤ በምድረ በዳም አበቦች ያብባሉ።

2 ምድረ በዳዎች በፈኩ አበቦች ይሞላሉ፤ የደስታ መዝሙርም ይዘምራሉ፤ እንደ ሊባኖስ ተራራ ግርማ ያላቸው ይሆናሉ፤ እንደ ቀርሜሎስም ተራራ ወይም እንደ ሻሮን ሸለቆ ክብርን የተጐናጸፉ ይሆናሉ። ሁሉም የእግዚአብሔርን ክብር የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ።

3 የደከሙትን ክንዶች አጠንክሩ፥ የተብረከረኩ ጒልበቶችንም አጽኑ።

4 ፈሪ ልብ ላላቸው “እነሆ አምላካችሁ ጠላቶቻችሁን ለመበቀልና የበደላቸውንም ዋጋ ለመክፈል መጥቶ ስለሚያድናችሁ በርቱ! አትፍሩ!” በሉአቸው።

5 በዚያን ጊዜ ዕውሮች ያያሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤

6 አንካሶች እንደ ሚዳቋ ይዘላሉ፤ መናገር የማይችሉ ድዳዎች ይዘምራሉ፤ በበረሓ ውስጥ የጅረት ውሃ ይፈስሳል።

7 የሚያቃጥለው አሸዋ ኩሬ ይሆናል፤ ደረቁም ምድር በምንጭ ውሃ ይረሰርሳል፤ የቀበሮዎች መፈንጫ የነበረው ስፍራ ለምለም ሣርና ቄጠማ የሚበቅልበት ይሆናል።

8 በዚያ “ቅዱስ ጐዳና” የሚባል መንገድ ይኖራል፤ እርሱም ለእግዚአብሔር ሰዎች ይሆናል፤ ንጹሕ ያልሆነ ሰው በዚያ መንገድ አይሄድም፤ ሞኞችም ሊሄዱበት አይችሉም።

9 አንበሶችም ሆነ ነጣቂ አውሬዎች በዚያ አይገኙም፤ በዚያ መንገድ የሚመላለሱ እግዚአብሔር የታደጋቸው ወገኖች ብቻ ይሆናሉ።

10 እግዚአብሔር የታደጋቸው ሰዎች ተመልሰው ይመጣሉ፤ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይገባሉ፤ ዘወትር የደስታን ዘውድ ይቀዳጃሉ፤ ተድላና ደስታንም ያገኛሉ፤ ማዘንና መቃተት ከእነርሱ ይርቃል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告