Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 33 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ርዳታ ለማግኘት የቀረበ ጸሎት

1 አንተ ማንም ጥፋት ሳያደርስብህ ጥፋተኛ የሆንክ! ማንም ሳይከዳህ ከዳተኛ የሆንክ ወዮልህ! ጥፋትን ማድረስህን ስታቆም ትጠፋለህ፤ ከዳተኛነትህንም ስታቆም ክዳት ይደርስብሃል።

2 አምላክ ሆይ! አንተን ተስፋ እናደርጋለንና ማረን! ማረን! በየቀኑ ጥበቃህ አይለየን፤ በመከራ ጊዜም ታደገን።

3 የአንተ ድምፅ እንደ መብረቅ በሚበርቅበት ጊዜ ሕዝቦች ይሸሻሉ፤ ከግርማህም የተነሣ መንግሥታት ይበተናሉ።

4 አንበጣ እንደሚሰበሰብ ምርኮ ይሰበሰባል፤ ኩብኩባዎች እንደሚዘሉ ሰዎች በምርኮው ላይ ይረባረባሉ።

5 እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ነው! በሰማያትም ይኖራል፤ ለጽዮንም ጽድቅንና ፍትሕን ያጐናጽፋል።

6 የሕዝቡ መሠረት እርሱ ነው፤ ለሕዝቡ ደኅንነትን፥ ጥበብንና ዕውቀትን ይሰጣል፤ እግዚአብሔርን መፍራትም ትልቁ ሀብታቸው ይሆናል።

7 ጀግኖች በመንገድ ላይ ለእርዳታ እንዴት እንደሚጮኹ፥ ለሰላም የተላኩትም መልእክተኞች እንዴት ምርር ብለው እንደሚያለቅሱ ተመልከቱ።

8 አውራ ጐዳናዎች ባዶ ሆኑ፤ በመንገዶቹ ላይ ተጓዦች የሉም፤ ቃል ኪዳን ፈረሰ፤ የውል ስምምነቶች ተጥሰዋል፤ ከዚህም የተነሣ ምክር የሚሰጠው ሰው አልተገኘም።

9 ምድሪቱም ደርቃለች፤ ባድማ ሆናለች፤ የሊባኖስ ደኖች ደርቀዋል፤ ለሙ የሳሮን ሸለቆ ወደ በረሓነት ተለውጦአል፤ በባሳንና በቀርሜሎስ ተራራዎች የሚገኙ ዛፎች ቅጠላቸው ረግፎአል።


እግዚአብሔር ለሚጠሉት ሁሉ የሰጠው ማስጠንቀቂያ

10 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አሁን እኔ እነሣለሁ፤ እከበራለሁ፤ ከፍ ከፍም እላለሁ።

11 ገለባን ፀንሳ እብቅ እንደምትወልድ እስትንፋሳችሁ እንደ እሳት ሆኖ ያጋያችኋል።

12 እናንተ ለኖራ እንደሚቃጠሉና ለእሳት እንደሚቈረጥ እሾኽ ትሆናላችሁ።

13 እናንተ በሩቅ ያላችሁ የሠራሁትን ስሙ፤ እናንተም በቅርብ ያላችሁ ኀያልነቴን አረጋግጡ።”

14 በጽዮን ያሉ ኃጢአተኞች ይፈራሉ፤ ከሐዲዎችም ይርበደበዳሉ፤ ከእኛ መካከል ከሚባላ እሳትና ከዘለዓለማዊ ነበልባል ጋር ለመኖር የሚችል ማነው ይላሉ።

15 በእውነትና በትክክል የሚናገሩ፥ በግፍ የሚገኝን ትርፍ የሚጸየፉ፥ ጉቦን ከመቀበል ይልቅ የሚያስወግዱ፥ ስለ ነፍስ ግድያ መስማት የማይፈልጉና፥ ክፉ ነገርን ከማየት ዐይኖቻቸውን የሚጨፍኑ፥

16 በከፍተኛ ቦታ ላይ ይኖራሉ። ከለላቸውም እንደ ቋጥኝ ምሽግ ይሆናል ምግባቸውንም በጊዜው ያገኛሉ፤ የሚጠጡትንም ውሃ አያጡም።


ወደፊት የሚመጣው ክብር የሞላበት ዘመን

17 በአራቱ ማእዘን ወሰንዋ በሰፊ ምድር ላይ ውበት ባለው ግርማ የሚያስተዳድረውን ንጉሥ ታያላችሁ፤

18 በሐሳባችሁ ቀድሞ ይደርስባችሁ የነበረውን ሽብር በማስታወስ “ኀላፊው የት አለ? ግብር ሰብሳቢው የት አለ? የዘብ ኀላፊውስ የት አለ?” ብላችሁ ትጠይቃላችሁ።

19 እናንተ ልታስተውሉትና ልትረዱት በማትችሉት ቋንቋ የሚንተባተቡባችሁን እብሪተኞች ባዕዳን ሕዝቦችን ከእንግዲህ ወዲህ አታዩአቸውም።

20 የታወቁ የሃይማኖት በዓላትን የምናከብርባትን የጽዮንን ከተማ ተመልከቱ፤ በሰላም ትኖሩባት ዘንድ ምቹ የሆነችውን ኢየሩሳሌምን እዩ! ካስማዎቹ ከቶ እንደማይነቀሉ፥ ገመዶቹም እንደማይበጠሱና ከስፍራው እንደማይንቀሳቀስ ድንኳን ትሆናለች።

21 እዚያም ማንም ጀልባዎችን በማይቀዝፍባቸውና ትላልቅ መርከቦች በማይንሳፈፉባቸው በወንዞችና በሰፋፊ ጅረቶች እግዚአብሔር በታላቅ ግርማው ከእኛ ጋር ይሆናል።

22 እግዚአብሔር ዳኛችን፥ ሕግ ሰጪአችንና ንጉሣችን ነው፤ የሚያድነንም እርሱ ነው፤

23 ሕዝባችሁ ግን የምሰሶው ገመድ እንደ ላላ ምሰሶውም እንዳልጸና፥ ሸራውም እንዳልተዘረጋ መርከብ ነው፤ ከዚያ በኋላ የተትረፈረፈ ምርኮ ይከፋፈላል፤ አንካሶች እንኳ ገብተው ይበዘብዛሉ።

24 ከጽዮን ነዋሪዎች መካከል “አመመኝ!” የሚል አይኖርም፤ በዚያም ለሚኖሩ ሁሉ የኃጢአት ይቅርታ ይደረግላቸዋል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告