ኢሳይያስ 31 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበግብጽ ላይ የመተማመን ከንቱነት 1 ብዙ ፈረሶች፥ ሠረገሎችና ወታደሮች ባሉት ብርቱ በሆነው በግብጽ ሠራዊት ተማምነው ርዳታ ለማግኘት ወደ ግብጽ ለሚወርዱ ወዮላቸው! ነገር ግን የእስራኤልን ቅዱስ ርዳታ አይለምኑም፤ መመሪያውንም አይቀበሉም። 2 ሆኖም እግዚአብሔር ጥበበኛ ነው፤ መቅሠፍትንም ያመጣል፤ ቃሉን አያጥፍም፤ በክፉ ሰዎች ቤት ላይና ክፉዎችን በሚረዱ ሰዎች ላይ ይነሣል። 3 ግብጻውያን ሰዎች ናቸው እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ ለባሾች እንጂ የተለዩ መናፍስት አይደሉም፤ እግዚአብሔር በቊጣው በሚነሣበት ጊዜ ይህ የሌሎች ረዳት የሆነው መንግሥት ይደናቀፋል፤ እርሱ ይረዳው የነበረውም መንግሥት ተንኰታኲቶ ይወድቃል፤ ሁለቱም በአንድነት ተያይዘው ይጠፋሉ። እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን የሚታደግ መሆኑ 4 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “አንበሳ በገደለው እንስሳ ላይ በሚያገሣበት ጊዜ እረኞች ተጠራርተው የቱንም ያኽል ቢጮኹ የእነርሱ ጩኸት ምንም እንደማያስፈራው እኔም የሠራዊት አምላክ የጽዮንን ተራራና ኰረብቶቿን ለመከላከል የሚያግደኝ የለም። 5 ወፍ በጎጆዋ ላይ ክንፍዋን ዘርግታ በማንጃበብ ጫጩቶችዋን እንደምትጠብቅ፥ እኔ የሠራዊት አምላክ ኢየሩሳሌምን እጋርዳታለሁ፤ እጠብቃታለሁ፤ አድናታለሁ፤ ከችግር አወጣታለሁ። 6 “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ፈጽማችሁ ወደ ከዳችሁኝ ወደ እኔ ተመለሱ! 7 በኃጢአተኛ እጃችሁ ከብርና ከወርቅ የሠራችኋቸውን ጣዖቶቻችሁን ሁሉ አሽቀንጥራችሁ የምትጥሉበት ጊዜ ይመጣል። 8 ከዚያ በኋላ አሦራውያን የሰው ባልሆነ ሰይፍ ይወድቃሉ። 9 ሽብር በተነሣ ጊዜ ምሽጋቸው ይፈርሳል፤ የጦር መኰንኖቻቸውም አርማቸውን ትተው በመርበድበድ ይሸሻሉ”። እሳቱ በጽዮን፥ እቶኑ በኢየሩሳሌም የሆነው እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል። |