Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 29 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የዳዊት ከተማ ለሆነችው ለኢየሩሳሌም ወዮላት

1 አሪኤል ተብላ ለምትጠራው ዳዊት ለሠፈረባት ለኢየሩሳሌም ከተማ ወዮላት! ዓመቶች ይደጋገሙ፤ በዓላትም በየዓመቱ ይከበሩ።

2 ከዚያ በኋላ ግን እኔ እግዚአብሔር “የእግዚአብሔር መሠዊያ” ተብላ የምትጠራውን የእስራኤል ከተማ አስጨንቃለሁ፤ እዚያም ሐዘንና የለቅሶ ዋይታ ይሆናል፤ ከተማይቱም በደም እንደ ተሸፈነ መሠዊያ ትሆናለች።

3 በዙሪያውም ግንብና ምሽግ ሠርቼ አስጨንቃታለሁ። በየመጠበቂያው ላይ ጠባቂዎችን አቆማለሁ። በቅጥርም መወጣጫ አሠራለሁ።

4 ካለችበት ከጥልቁ ጒድጓድ ትናገራለች፤ ከታች ከትቢያ ውስጥ ንግግርዋ ይመጣል፤ ድምፅዋም እንደ ምትሐት ከምድረ በዳ ይወጣል፤ ከአዋራ ውስጥም ዝቅ ያለ ድምፅዋ ይሰማል።

5 ኢየሩሳሌም ሆይ! በአንቺ ላይ በጠላትነት የሚነሡ የጠላት ሠራዊት ሁሉ እንደ ትቢያ በነው ይጠፋሉ፤ እጅግ የሚያስፈሩ ሠራዊቶቻቸውም ሳይታሰቡ በድንገት በነፋስ እንደሚወሰድ ገለባ ይሆናሉ።

6 የሠራዊት ጌታ አምላክ ነጐድጓድን፥ የመሬት መናወጥን፥ ታላቅ ድምፅን፥ ዐውሎ ነፋስን፥ ሞገድንና የሚባላ የእሳት ነበልባልን በጠላቶችሽ ላይ በመላክ አንቺን ይታደግሻል።

7 የእግዚአብሔር መሠዊያ የሆነችውን ከተማ ለማጥቃት የሚመጡ የመንግሥታት ሠራዊቶች ሁሉ ከነጦር መሣሪያዎቻቸው ይደመሰሳሉ፤ እንደ ሕልም ወይም በእንቅልፍ ልብ እንደሚታሰብ ነገር የተረሱ ይሆናሉ።

8 በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ በመጣል የተሰበሰቡ መንግሥታት ሁሉ በሕልሙ ሲበላ ዐድሮ ጠዋት በነቃ ጊዜ ምንም ያልቀመሰ ረኃብተኛ መሆኑንና እንዲሁም በሕልሙ ሲጠጣ ዐድሮ ጧት በነቃ ጊዜ ጒሮሮው በውሃ ጥም ደርቆ እንደሚያገኘው ሰው ይሆናሉ።


የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መናቅ የሚያስከትለው ቅጣት

9 እንደ ደነቈራችሁና እንደ ታወራችሁ ቅሩ! ምንም ወይን ጠጅ ሳትጠጡ የሰከራችሁ ሁኑ! ምንም ዐይነት የሚያሰክር መጠጥ ሳትቀምሱ ተንገዳገዱ!

10 እግዚአብሔር ከባድ እንቅልፍ ስለ ጣለባችሁ እናንተ ነቢያት ዐይኖቻችሁን ጨፍናችኋል፤ እናንተም ባለ ራእዮች አእምሮአችሁን ዘግታችኋል።

11 የትንቢት ራእይ ሁሉ ትርጒም ከእናንተ ተሰውሮ እንደ ታሸገ መጽሐፍ ይሆናል፤ ወደሚያነብ ሰው ወስዳችሁ “አንብብልን” ብላችሁ ብትጠይቁት እንኳ “ስለ ታሸገ ላነበው አልችልም” ይላችኋል።

12 ማንበብ ወደማይችል ሰው ወስዳችሁ “አንብብልን” ብትሉት፥ “እኔ ማንበብ አልችልም” ይላችኋል።

13 ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ሕዝብ በአፉ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ እኔንም የሚያመልከኝ ሰው ሠራሽ ወግና ሥርዓትን እያስተማረ በከንቱ ነው።

14 አስደናቂ ተአምርን አከታትዬ በማምጣት ይህ ሕዝብ እንዲገረም አደርገዋለሁ፤ የጥበበኞች ጥበብ ትሰወራለች፤ የአስተዋዮችም ማስተዋል ትረሳለች።”


የወደፊቱ ተስፋ

15 ዕቅዳቸውን ከእግዚአብሔር ለመደበቅ ወደ ጥልቅ ቦታ ለሚሄዱ በጨለማ የሠሩትንም ሥራ “ማን ያይብናል? ማን ያውቅብናል?” ለሚሉ ሰዎች ወዮላቸው!

16 እናንተ ሁሉን ነገር ትገለባብጣላችሁ። ሸክላ ሠሪው ከሸክላው አይበልጥምን? አንድ የተሠራ ሥራ ሠሪውን “አንተ አልሠራኸኝም” ይለዋልን? ወይስ ደግሞ የሸክላ ዕቃ ሸክላ ሠሪውን “ሥራህን አታውቅም” ይለዋልን?

17 በጥቂት ጊዜ ውስጥ የሊባኖስ ጫካ የእርሻ ቦታ ይሆናል፤ የእርሻው ቦታ ወደ ጫካነት ይለወጣል።

18 ደንቆሮዎች የሚነበብላቸውን መጽሐፍ መስማት የሚችሉበት ጊዜና በጨለማ የሚኖሩ ዕውሮችም ዐይኖቻቸው በርተው የሚያዩበት ጊዜ ይመጣል።

19 ትሑታንና ችግረኞች በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ይደሰታሉ።

20 ጨካኞችና ፌዘኞች ይጠፋሉ፤ ክፉ አድራጊዎችም ሁሉ ይደመሰሳሉ።

21 ሰውን በነገር ወንጀለኛ የሚያደርጉ፥ ተከሳሽንም በፍርድ ሸንጎ የሚያጠምዱ፥ በሐሰተኛ ምስክር ንጹሕ ሰው ፍትሕ እንዳያገኝ በሐሰት የሚመሰክሩትን ሁሉ እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል።

22 ስለዚህ አብርሃምን ከችግሩ ያዳነ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤ ሆይ! ከእንግዲህ ወዲህ ውርደትና ኀፍረት አይደርስባችሁም።

23 የእጄ ሥራ የሆኑትን ልጆቻቸውን በመካከላቸው ባዩ ጊዜ ስሜን ይቀድሳሉ፤ የእስራኤልን ቅዱስ ያከብራሉ፤ በእስራኤልም አምላክ ፊት በፍርሃት ይቆማሉ።

24 በመንፈስም የሚሳሳቱ ማስተዋልን ይገበያሉ፤ ዘወትር የሚያጒረመርሙ ትምህርትን ይቀበላሉ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告