Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 27 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 በዚያን ቀን እግዚአብሔር በጽኑ፥ በታላቁና በኀያል ሰይፉ የሚስለከለከውንና የሚጠመጠመውን እባብ ሌዋታንን ይቀጣል፤ የባሕሩንም ዘንዶ ይገድላል።

2 በዚያን ጊዜ ፍሬአማ ለሆነው የወይን ተክል ቦታ ዘምሩለት፤

3 እኔ እግዚአብሔር እጠብቀዋለሁ በየጊዜውም ውሃ አጠጣዋለሁ፤ ማንም ሰው እንዳይጐዳው ሌሊትና ቀን እጠብቀዋለሁ።

4 ዳግመኛ በወይን ቦታዬ ላይ አልቈጣም፤ የወይን ቦታዬን የሚያበላሹ ኲርንችትና እሾኽ ቢኖሩ ነቃቅዬ በእሳት በማቃጠል ፈጽሞ አጠፋቸዋለሁ።

5 ሆኖም የአትክልቱ ቦታ በእኔ ጥበቃ ከተማመነ እርሱ ወዳጄ ይሆናል፤ ከእኔም ጋር በሰላም ይኖራል።

6 በሚመጡት ዘመናት የያዕቆብ ዘር የሆኑ የእስራኤል ሕዝብ እንደ ወይን ግንድ ሥር ይሰዳሉ፤ አብበውም ያፈራሉ፤ ፍሬአቸውም ምድርን ይሞላል።

7 እስራኤል የተቀጣችው ጠላቶችዋ በእግዚአብሔር የተቀጡትን ያኽል አይደለም፤ የጠላቶችዋንም ያኽል ብዙ ሰው አልተገደለባትም።

8 እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ ምርኮ እንዲሰደዱ በማድረግ ቀጣቸው፤ እንደ ኀይለኛ የምሥራቅ ዐውሎ ነፋስም አባረራቸው።

9 እንግዲህ የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ለኃጢአታቸው ይቅርታ ማግኘት የሚችሉት የአሕዛብን የመሠዊያ ድንጋዮች እንደ ኖራ ፈጭተው፥ የዕጣን መሠዊያዎችንም ሆነ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስሎች ሲያስወግዱ ነው።

10 የተመሸገችው ከተማ ፈራርሳለች፤ ባዶዋን ቀርታ ጭው ያለ ምድረ በዳ መስላለች፤ የከብቶች መሰማሪያ ስለ ሆነች በዚያ ጥጆች የዛፍ ቅርንጫፎችን እየበሉ ያርፋሉ።

11 የዛፍ ቅርንጫፎች በሚደርቁበትም ጊዜ ይሰባበራሉ፤ ሴቶችም ለእሳት ማገዶ ይለቅሙአቸዋል፤ ሕዝቡ ማስተዋል ስለ ጐደለው ፈጣሪ አምላኩ አይራራለትም፤ ምንም ምሕረት አያደርግለትም።

12 ገበሬ ስንዴውን ከገለባ እንደሚለይ በዚያን ቀን ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ እስከ ግብጽ ወሰን ድረስ ያሉትን ሕዝቡን እስራኤልን እግዚአብሔር አንድ በአንድ ይሰበስባል።

13 በዚያም ዘመን ትልቅ መለከት ይነፋል፤ በአሦር ምድር ጠፍተው የነበሩትና ወደ ግብጽ ተሰደው የነበሩት እስራኤላውያንም ተመልሰው በኢየሩሳሌም በሚገኘው በተቀደሰው ተራራ ላይ ይሰግዳሉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告