Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 25 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የምስጋና መዝሙር

1 አምላክ ሆይ! አንተ አምላኬ ነህ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ስምህንም አመሰግናለሁ፤ አንተ እጅግ አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን አድርገሃል፤ ከጥንት ጀምሮ ያቀድከውን ሁሉ፥ ፍጹምነት ባለው አስተማማኝ ሁኔታ አከናውነሃል።

2 ከተሞች ፈርሰው ባድማ እንዲሆኑ አድርገሃል፤ ምሽጎቻቸውንም አፈራርሰሃል፤ ጠላቶቻችን የሠሩአቸው ቤተ መንግሥቶች እንዳልነበሩ ሆነዋል፤ እስከ ዘለዓለምም እንደገና አይሠሩም።

3 የታላላቅ መንግሥታት ሕዝቦች ያከብሩሃል፤ በጨካኞች መንግሥታት ከተሞች የሚኖሩ ሁሉ ይፈሩሃል።

4 ለድኾች፥ ለመጻተኞችና ለችግረኞች በችግራቸው ጊዜ መጠጊያ ሆነህላቸዋል፤ ከዐውሎ ነፋስ የሚድኑበት ተገንና ከፀሐይ ቃጠሎ የሚጠለሉበት ጥላ ሆነህላቸዋል፤ የጨካኞች ምት የክረምት ወጀብ ግድግዳን እንደሚገፋ ያለ ነው።

5 እነርሱ በደረቅ ቦታ ላይ እንዳለ ሙቀት ሕዝብን ይጐዳሉ፤ አምላክ ሆይ! አንተ ግን የባዕዳንን ድንፋታ ዝም አሰኘህ፤ የደመና ጥላ ቃጠሎን እንደሚያበርድ የጋጠወጦችን ዘፈን ጸጥ አደረግህ።


እግዚአብሔር የሚያዘጋጀው ታላቅ ግብዣ

6 የሠራዊት አምላክ በዚህች በጽዮን ተራራ ለዓለም ሕዝቦች ሁሉ ታላቅ ግብዣ ያዘጋጃል፤ በግብዣውም ላይ ምርጥ የወይን ጠጅና፥ የተሟላ ምግብ ይዘጋጃል።

7 በዚህ ተራራ ላይ ሕዝቦችን ሁሉ ጋርዶ የነበረውን የሐዘን መጋረጃ ያስወግዳል።

8 ልዑል እግዚአብሔር የሞትን ኀይል ለዘለዓለም ያጠፋል! ከሰዎችም ሁሉ ዐይን እንባን ያብሳል፤ ወገኖቹ በዓለም ሁሉ ላይ የተቀበሉትን ኀፍረት ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ራሱ ይህን ተናግሮአል።

9 ይህም በሚፈጸምበት ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ “እነሆ፥ እርሱ አምላካችን ነው፤ በእርሱ ስለ ታመንን አድኖናል፤ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ እኛም በእርሱ ታምነናል፤ እርሱ ስለ ታደገን በደስታ ተሞልተን ሐሴት እናደርጋለን!” ይላሉ።


እግዚአብሔር ሞአብን እንደሚቀጣ

10 የእግዚአብሔር ኀይል የጽዮንን ተራራ ይጠብቃል። የሞአብ ሕዝብ ጭድ ከጭቃ ጋር በጒድጓድ ውስጥ እንደሚረገጥ ይረገጣሉ።

11 እንደ ዋነተኛ እጆቻቸውን ይዘረጋሉ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በትዕቢታቸው ስለሚያዋርዳቸው እጆቻቸው ይዝለፈለፋሉ።

12 የሞአብን ምሽጎች ከታላላቅ ግንቦቻቸው ጋር ያፈራርሳል፤ ተሰባብረውም ከትቢያ ጋር ይቀላቀላሉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告