ኢሳይያስ 24 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእግዚአብሔር ቊጣ በምድር ላይ 1 እነሆ እግዚአብሔር ምድሪቱን አፈራርሶ ባድማ ያደርጋታል፤ የዚያችንም ምድር ገጽታ ለዋውጦ ሕዝቦችዋን ይበትናል፤ 2 የሰው ሁሉ ዕድል አንድ ዐይነት ይሆናል፤ ካህናትና ሕዝቡ፥ አገልጋዮችና አሳዳሪዎቻቸው፥ እመቤቲቱና አገልጋይቱ፥ ገዢዎችና ሻጮች፥ አበዳሪዎችና ተበዳሪዎች፥ ዕዳ ከፋይና ዕዳ አስከፋይ በአንድነት ይጠፋሉ። 3 ምድሪቱ ተበዝብዛ ባዶዋን ትቀራለች፤ ይህ ሁሉ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ስለ ሆነ ይፈጸማል። 4 ምድሪቱ እጅግ ደርቃ ልምላሜዋ ሁሉ ይጠወልጋል፤ የምድርም ታላላቅ ሰዎች ይደክማሉ። 5 ሰዎች ሕጎችን በመጣስ፥ ደንብን በመተላለፍና ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በማፍረስ ምድርን አርክሰዋል። 6 ስለዚህም ርግማን ምድርን ያጠፋል፤ ሕዝቦችዋም በበደሉት በደል ተጠያቂዎች ይሆናሉ፤ ስለዚህ የምድር ነዋሪዎች ይደመሰሳሉ፤ የሚተርፉትም ጥቂቶች ናቸው። 7 የወይን ተክሎች ደርቀዋል፤ የወይን ጠጅም ተወዶአል፤ በዚህ ምክንያት ከዚህ በፊት ይደሰት የነበረ ሁሉ አሁን ሐዘንተኛ ሆኖአል፤ 8 የሚያስደስት የመሰንቆ፥ ሙዚቃና የአታሞ ድምፅ መሰማቱ ቀርቶአል፤ የበዓል አከባበር ሁሉ ቆሞአል። 9 የወይን ጠጅ እየጠጡ በመዝፈን መደሰት አይኖርም፤ የሚያሰክር መጠጥም ለጠጪው መራራ ይሆናል። 10 የፈረሰችው ከተማ ባድማ ትሆናለች፤ ማንም ሰው እንዳይገባበት ቤቱ ሁሉ ተዘግቶአል። 11 ዳግመኛ የወይን ጠጅ ስለማይገኝ ሰዎች በየአደባባዩ ይጮኻሉ፤ ደስታ ለዘለዓለም ጠፍቶአል፤ ሐሴትም በምድር ላይ አይገኝም፤ 12 ከተማይቱ የፍርስራሽ ክምር ሆናለች፤ በሮችዋም ተሰባብረው ወድቀዋል። 13 በዓለም መንግሥታት ሁሉ ላይ የሚደርሰው ሁኔታ ይህ ነው፤ የወይራ ፍሬ ከዛፍ ሁሉ ላይ ተለቅሞ፥ የወይንም ዘለላ ከተሰበሰበ በኋላ እንደሚታይ የመከር መጨረሻ ይሆናል። 14 ከጥፋት የተረፉት በደስታ እልል ይላሉ፤ በስተ ምዕራብ ያሉትም ሁሉ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ይናገራሉ። 15 ስለዚህ በምሥራቅ ያሉት ለእግዚአብሔር ክብር ይሰጣሉ፤ በደሴቶች ያሉ ሁሉ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ስም ከፍ ከፍ ያደርጋሉ። 16 “ለጻድቁ ለእርሱ ክብር ይሁን!” የሚል መዝሙር ከዓለም ዳርቻ ይሰማል። እኔ ግን እጅግ በመክሳት ስለ መነመንኩ ወዮልኝ! ከዳተኞች በከዳተኝነታቸው ጸንተዋል፤ ከዳተኛነታቸውም እየባሰ ሄዶአል። 17 በምድር ላይ የምትኖሩ ሁሉ! አድምጡኝ! ሽብር፥ ጒድጓድና ወጥመድ ይጠብቃችኋል። 18 ከአሸባሪ ድምፅ የሚሸሽ በተቈፈረ ጒድጓድ ውስጥ ይወድቃል፤ ከጒድጓድ ዘሎ ለማምለጥ የሚሞክርም በወጥመድ ይያዛል፤ ከሰማይ ብርቱ ዝናብ ይዘንባል፤ የምድር መሠረቶችም ይናወጣሉ። 19 ምድር ተናወጠች፤ ተሰነጣጥቃም ተከፋፈለች። 20 ምድር እንደ ሰከረ ሰው ትንገዳገዳለች፤ በዐውሎ ነፋስ እንደ ተገፋ ጎጆም ትናወጣለች፤ እርስዋም የኃጢአትዋ ሸክም ስለሚጫናት ትወድቃለች፤ መነሣትም አትችልም። 21 እግዚአብሔር በዚያን ዘመን የሰማይ ኀይላትንና የምድር ገዢዎችን የሚቀጣበት ጊዜ ይመጣል። 22 እግዚአብሔር ነገሥታትን በአንድነት ሰብስቦ በምድር ውስጥ ባለ እስር ቤት ውስጥ እንዳሉ እስረኞች እንዲኖሩ ያደርጋል፤ ከብዙ ቀኖችም በኋላ ይቀጣቸዋል። 23 የሠራዊት እምላክ ስለሚነግሥ ጨረቃ ትጨልማለች፥ ፀሐይም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ እርሱ በኢየሩሳሌም፥ በጽዮን ተራራ ላይ ሆኖ ያስተዳድራል፤ የሕዝቡ መሪዎች ሁሉ ክብሩን ያያሉ። |