ኢሳይያስ 23 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምስለ ጢሮስ የተነገረ ትንቢት 1 ስለ ጢሮስ ከተማ የተነገረ የትንቢት ቃል ይህ ነው፤ ጢሮስና ቤትዋ ወይም ወደብዋ የፈራረሱ ስለ ሆነ እናንተ የተርሴስ መርከቦች እሪ በሉ፤ ከቆጵሮስ ስትመለሱ የሚጠብቃችሁ ወሬ ይኸው ነው። 2 መርከበኞች ያበለጸጉአችሁ እናንተ የደሴቲቱ ሕዝብና የሲዶን ነጋዴዎች በሐዘን ጸጥ በሉ! 3 በግብጽ የሚመረተው እህል በትልቁ ባሕር በኩል መጥቶ ለጢሮስ ትልቅ ገቢ ይሆናል፤ ስለዚህ ጢሮስ የዓለም ገበያ ሆናለች። 4 የሲዶና ከተማ ሆይ! አንቺ በባሕር አጠገብ የተገነባሽ ጠንካራ ምሽግ ነሽ፤ ነገር ግን አንቺ ባል አግብታ ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወልዳ እንዳላሳደገች ሴት የተዋረድሽ ትሆኚአለሽ። 5 ጢሮስ መደምሰስዋን በሰሙ ጊዜ ግብጻውያን በድንጋጤ ይታወካሉ። 6 እናንተ በባሕር ጠረፍ የምትኖሩ ሕዝብ ሆይ! በዋይታ እያለቀሳችሁ ወደ ተርሴስ ተሻገሩ። 7 ሕዝቦችዋ ወደ ሩቅ አገር ሄደው ለመስፈር የቻሉት ለዘመናት ተደስታ ትኖር የነበረችው ከተማ እንዲህ ሆና ቀረችን? 8 ዘውድን ታቀዳጅ በነበረችው ከተማ፥ ልዑላን የሆኑና በዓለም የተከበሩ ነጋዴዎች በነበርዋት በጢሮስ ላይ ይህን ሁሉ ያቀደ ማነው? 9 ይህንማ ያቀደው የሠራዊት አምላክ ነው፤ እርሱም ይህን ያቀደው ባደረጉት ነገር መታበያቸውን እንዲተዉ ለማድረግና የተከበሩትንም ሰዎች ለማዋረድ ብሎ ነው። 10 የተርሴስ ሕዝብ ሆይ! ከእንግዲህ ወዲያ ወደብ ስለሌላችሁ ልክ በአባይ ወንዝ ዳር እንደሚደረገው ምድራችሁን እረሱ። 11 መንግሥታትን በማናወጥ የእግዚአብሔር ኀይል እስከ ባሕር ማዶ ደርሶአል፤ በከነዓንም ምድርም ያሉ ምሽጎች እንዲፈርሱ አዞአል። 12 “አንቺ የሲዶን ከተማ ሆይ! የደስታሽ ዘመን አክትሞአል፤ ሕዝብሽ ተጨቊነዋል፤ ወደ ቆጵሮስ ሸሽተው ቢያመልጡ እንኳ እዚያ በሰላም አይኖሩም” ብሎአል። 13 እነሆ የባቢሎናውያንን ምድር ተመልከቱ፤ ሕዝቡ ዋጋቢስ ሆኖ ቀርቶአል፤ አሦራውያን ምድሪቱን የአራዊት መፈንጫ አድርገዋታል፤ ምሽጎችዋንም ሰባብረው፥ ምድሪቱን የፍርስራሽ ክምር በማድረግ የራሳቸውን ምሽግ አቁመውባታል። 14 እናንተ በባሕር ላይ የምትመላለሱ የተርሴስ መርከበኞች! የምትኰሩባት ወደብ ስለ ተደመሰሰች በዋይታ አልቅሱ! 15 ጢሮስ ሰባ ዓመት ያኽል ተረስታ የምትኖርበት ጊዜ ይመጣል፤ ይህም የአንድ ንጉሥ ዕድሜ ነው፤ እነዚያ ዓመቶች ካለፉ በኋላ ጢሮስ እንደ ዘማዊት ሴት እንዲህ ተብሎ ቅኔ የሚነገርባት ትሆናለች፦ 16 አንቺ የተረሳሽ ዘማዊት በገናሽን እየደረደርሽ በከተማ ውስጥ ዙሪ! እንዲያስታውሱሽ ጣዕመ ዜማ አሰሚ፤ ብዙ መዝሙሮችንም ዘምሪ! 17 ከሰባ ዓመት በኋላ እግዚአብሔር ጢሮስን ይጐበኛታል፤ ወደ ቀድሞ የንግድ ሥራዋ እንድትመለስ ያደርጋታል፤ በምድር ላይ ከሚገኙ መንግሥታት ሁሉ ጋር ታመነዝራለች። 18 በንግድ የምታገኘውም ገንዘብ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናል፤ ለራስዋ ተቀማጭ ሳታደርግ የእግዚአብሔር አገልጋዮች በሚያስፈልጋቸው ምግብና በጥሩ ልብስ ያውሉታል። |