ኢሳይያስ 22 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምስለ ኢየሩሳሌም የተነገረ ቃል 1 “የራእይ ሸለቆ” ተብሎ ስለሚጠራው ቦታ የተነገረ ቃል ይህ ነው፤ በየቤታችሁ ሰገነት ላይ ሆናችሁ በዓል የምታከብሩት በምን ምክንያት ነው? 2 በሁካታና በጩኸት የተሞላሽ አንቺ ከተማ ሆይ! ሰክረው በመንገዶችሽ ላይ የወደቁት ሰዎች በሰይፍ የተገደሉ ወይም በጦርነት የሞቱ አይደሉም። 3 መሪዎችሽ በሙሉ አንዲት ፍላጻ ሳይወረውሩ በሽሽት ላይ እንዳሉ ተማረኩ። 4 ስለ ሞቱት ሕዝቦቼ በመረረ ሁኔታ አለቅስላቸው ዘንድ ተዉኝ፤ አታጽናኑኝ። 5 ይህ በራእይ ሸለቆ የጭንቅ፥ የመረገጥ፥ የሽብር ጊዜ ነው፤ ይህ ሁሉ በእኛ ላይ እንዲፈጸም የፈቀደው የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው፤ የከተማችን ቅጽሮች ፈራርሰው ወድቀዋል፤ ርዳታ ለማግኘት የሚደረገውም ጩኸት እስከ ተራራዎች በማስተጋባት ላይ ነው። 6 የዔላም አገር ወታደሮች በሠረገላና በፈረስ ተቀምጠው ቀስትና ፍላጻ አንግበው መጡ፤ የቂር ወታደሮች ጋሻቸውን አዘጋጅተዋል። 7 የይሁዳ ለምለም ሸለቆዎች በሠረገሎች የተሞሉ ሆነዋል። ፈረሰኞች በኢየሩሳሌም ቅጽር በር ፊት ለፊት ቆመዋል። 8 የይሁዳ ምሽጎች ሁሉ ተደምስሰዋል፤ በዚያን ጊዜ በጦር ግምጃ ቤት ውስጥ የተከማቸውን የጦር መሣሪያ ወሰዳችሁ። 9 የዳዊት ከተማ ብዙ ፍርስራሾች መብዛታቸውን ተመልክታችኋል፤ ከታችኛውም ኩሬ ውሃ አጠራቀማችሁ። 10 በኢየሩሳሌም ያሉትን ቤቶች ሁሉ እየተዘዋወራችሁ ቈጠራችሁ፤ ቅጥሩን ለማደስ አንዳንዶቹን ቤቶች አፈረሳችሁ። 11 ከጥንቱ ኲሬ የሚወርደውን ውሃ ለመመለስ በከተማይቱ ውስጥ ግድብ ሠራችሁ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በመጀመሪያ ዐቅዶ ያደረገው እግዚአብሔር መሆኑ ትዝ አላላችሁም። 12 በዚያን ጊዜ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ጠጒራችሁን ተላጭታችሁ፥ ማቅም ለብሳችሁ እንድታዝኑና እንድታለቅሱ ጠርቶአችሁ ነበር፤ 13 እናንተ ግን ጥሪውን በመቀበል ፈንታ በዓል አደረጋችሁ፤ የምትበሉትንም በግና በሬ ዐረዳችሁ፤ ወይን ጠጅም ጠጥታችሁ “ነገ እንሞታለን ዛሬ እንብላ እንጠጣ!” አላችሁ። 14 የሠራዊት አምላክ እንዲህ ብሎ ነግሮኛል፦ “በሕይወት እስካሉ ድረስ ይህ ክፉ በደል አይሰረይላቸውም፤ እኔ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” ለሼብና የተሰጠ ማስጠንቀቂያ 15 የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር በንጉሡ ቤተ መንግሥት መጋቢ ሆኖ ወደ ተሾመው ወደ ሼብና ሄደህ እንዲህ በለው አለኝ፤ 16 “ሼብና ሆይ! በኰረብታ ላይ መቃብርህን፥ በአለቱም መኖሪያህን ድንጋይ ጠርበህ ለመሥራት ማን መብት ሰጠህ? 17 ‘እኔ ኀያል ሰው ነኝ’ ትል ይሆናል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አንሥቶ ይወረውርሃል። 18 እርሱም ወደምትሞትበትና ሠረገሎችህም ቆመው ወደሚቀሩበት ቦታ እንደ ኳስ ጠቅልሎ ወደ ሰፊው ሜዳ ይወረውርሃል፤ ለጌቶችህም ኀፍረት ትሆናለህ። 19 እግዚአብሔር አንተን ከደረጃህ ዝቅ ያደርግሃል፤ ከሥራህም ያባርርሃል። 20 “በዚያን ጊዜ አገልጋዬን የሕልቂያን ልጅ ኤልያቄምን አስጠራዋለሁ፤ 21 የአንተ የነበረውን የማዕርግ ልብስ አለብሰዋለሁ፤ መታጠቂያህንም እሰጠዋለሁ፤ የአንተ የነበረውንም ሥልጣን ሁሉ ለእርሱ አስረክባለሁ፤ እርሱ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሕዝቦች እንደ አባት ይሆናል። 22 የዳዊትን ቤት የቊልፍ መክፈቻ እሰጠዋለሁ፤ እርሱ የሚከፍተውን መዝጋት፥ የሚዘጋውንም መክፈት የሚችል አይኖርም። 23 እኔ እርሱን ኲላብ ተብሎ እንደሚጠራ እንደ ጠንካራ የዕቃ መስቀያ አደርገዋለሁ፤ ለቤተሰቡ ሁሉ የክብር መገኛ ይሆናል። 24 “ነገር ግን ቤተ ዘመዶቹና የሩቅ ዘመዶቹ የሆኑ ሁሉ እንደ ከባድ ሸክም ይሆኑበታል፤ ከሲኒ አንሥቶ እስከ እንስራ ያሉት የቤት ዕቃዎች ሁሉ በኲላብ ላይ እንደሚሰቀሉ እነርሱም በእርሱ ላይ የሚንጠለጠሉ ይሆናሉ። 25 በዚያም ቀን የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ ‘ይህ ሁሉ ነገር በሚፈጸምበት ጊዜ ግን ጠንካራው የዕቃ መስቀያ ኲላብ ተነቅሎ ይወድቃል፤ በኲላቡም ላይ ተሰቅሎ የነበረው ዕቃ ሁሉ ተሰባብሮ ይወድቃል።’ ” ይህን የተናገረ እግዚአብሔር ነው። |