Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የባቢሎንን አወዳደቅ የሚያመለክት ራእይ

1 በባሕር አጠገብ ስለሚገኝ ምድረ በዳ የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። ከደቡብ በኩል የሚመጣው ዐውሎ ነፋስ ሁሉን ነገር ጠራርጎ እንደሚወስድ አስፈሪ ከሆነች ከአንዲት አገር ከባድ ጥፋት ይመጣል።

2 አስፈሪ የሆነ ራእይ ተገልጦልኛል፤ ይኸውም አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፤ ከዳተኛው ይከዳል፤ ዘራፊውም ይዘርፋል። የዔላም ሠራዊት ሆይ! አደጋ ለመጣል ውጡ! የሜዶን ሠራዊት ሆይ! ከተሞችን ክበቡ! እግዚአብሔር በባቢሎን ምክንያት የደረሰውን ሥቃይ ሁሉ ያስወግዳል።

3 በዚህም ምክንያት ሰውነቴ ታመመ፤ ምጥ እንደ ያዛት ሴትም አስጨነቀኝ፤ በምሰማው ነገር ታወክሁ፤ በማየውም ነገር ግራ ተጋባሁ።

4 ራሴን ያዞረኛል፤ ከፍርሃት የተነሣም እንቀጠቀጣለሁ፤ ቀኑ ቶሎ እንዲመሽልኝ ተመኘሁ፤ ተስፋ ያደረግኹት ጭላንጭል አስደንጋጭ ሆነብኝ፦

5 ባየሁትም ራእይ ግብዣ ተዘጋጅቶ ለእንግዶች መቀመጫ ስጋጃዎች ተነጥፈዋል፤ እነርሱም ገና በመብላትና በመጠጣት ላይ ሳሉ፥ “እናንተ የጦር መኰንኖች! ጋሻችሁን ወልውላችሁ አዘጋጁ!” የሚል ድንገተኛ ትእዛዝ ተላለፈላቸው።

6 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ሂድ ሁኔታውን ሁሉ እያጠና የሚገልጥልህ ተመልካች መድብ።

7 ፈረሰኞች ጥንድ ጥንድ ሆነው ሲጋልቡ፥ የአህያና የግመል ጋላቢዎችንም ቢያይ በጥንቃቄ ይመልከታቸው።”

8 ዘብ ጠባቂው “ጌታዬ ሆይ! እኔ በማማዬ ላይ ሆኜ ሌት ከቀን በመጠበቅ ላይ ነኝ” ይላል።

9 ጥንድ ጥንድ ሆነው በፈረስ የተቀመጡ ሰዎች እነሆ በድንገት ይመጣሉ፤ ዘብ ጠባቂውም “እነሆ ባቢሎን ወደቀች! የሚሰግዱላቸውም ጣዖቶች ሁሉ ተሰባብረው ወደቁ” የሚል ዜና ያስተላልፋል።

10 ሕዝቤ እስራኤል ሆይ! ስንዴ በአውድማ ላይ እንደሚወቃ እናንተም ተወቅታችሁ ነበር፤ አሁን ግን የሠራዊት ጌታ፥ የእስራኤል አምላክ፥ የሰማሁትን የምሥራች ቃል ገለጥሁላችሁ።


ስለ ኤዶም የተነገረ ቃል

11 ስለ ኤዶም የተነገረ ቃል ይህ ነው፤ አንድ ሰው ከኤዶም በኩል ሆኖ “ዘብ ጠባቂ ሆይ! ሌሊቱ መቼ ይነጋ ይሆን? ሌሊቱ ሊነጋ ምን ያኽል ጊዜ እንደ ቀረው ንገረኝ” ይላል።

12 ዘብ ጠባቂውም “በእርግጥ የሌሊቱ ንጋት እየተቃረበ ነው፤ ነገር ግን ሌሊቱ ተመልሶ ይመጣል፤ እንደገና ጠይቀህ ለመረዳት ብትፈልግ ተመልሰህ ናና ጠይቅ” አለው።


ስለ ዐረብ አገር የተነገረ ቃል

13 ስለ ዐረብ አገር የተነገረውም ቃል ይህ ነው፤ ከጭነት ግመሎቻችሁ ጋር በዐረብ በረሓ የምትሰፍሩ እናንተ የደዳን ሕዝብ ሆይ፥

14 ተጠምተው ወደ እናንተ ለሚመጡት ሁሉ ውሃ ስጡአቸው፤ እናንተም የቴማ ሕዝብ ሆይ! ለስደተኞች ምግብ አቅርቡላቸው።

15 ሕዝቡ ሁሉ ከሚገደሉበት ሰይፍ፥ ከተደገነባቸው ቀስትና ከጦርነት አደጋ ሁሉ ለማምለጥ በመሸሽ ላይ ናቸው።

16 ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “የሠራተኞች የሥራ ውል እንደሚያልቅ ልክ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የቄዳር ነገዶች ክብር ይወገዳል፤

17 ከቄዳር አርበኞች የሚተርፉት ቀስተኞች ጥቂቶች ናቸው። እኔ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ይህን ተናግሬአለሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告