ኢሳይያስ 20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእርቃኑን የሚሄደው ነቢይ ምልክትነት 1 የአሦር ንጉሠ ነገሥት በሆነው በሣርጎን ትእዛዝ የአሦራውያን ጦር አዛዥ የፍልስጥኤማውያን ከተማ በሆነችው በአሽዶድ ላይ አደጋ ጣለ፤ 2 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር የአሞጽን ልጅ ኢሳይያስን “ጫማህንና የማቅ ልብስህን አውልቀህ በባዶ እግርህ ሂድ” ብሎ አዘዘው። ኢሳይያስም ለቃሉ በመታዘዝ ዕራቊቱን በባዶ እግሩ ይመላለስ ነበር። 3 እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “አገልጋዬ ኢሳይያስ ዕራቊቱን በባዶ እግሩ ሦስት ዓመት ሙሉ ሲመላለስ ነበር፤ በግብጽና በኢትዮጵያ ላይ የሚደርስባቸውም ምልክት ይኸው ነው። 4 የአሦር ንጉሠ ነገሥት ለግብጻውያን ኀፍረት ይሆን ዘንድ መቀመጫዎቻቸው ሳይሸፈኑ ወጣቶችም ሆኑ ሽማግሌዎች ዕራቊታቸውንና ባዶ እግራቸውን ሆነው ግብጾችንና ኢትዮጵያውያንን በምርኮ ይመራቸዋል። 5 በኢትዮጵያ የሚተማመኑና በግብጽም የሚመኩ ሁሉ ግራ ተጋብተው ተስፋ ይቈርጣሉ። 6 በዚያን ጊዜ በባሕር ዳርቻ የሚኖሩ ሰዎች፦ ‘እኛን ከአሦር ንጉሠ ነገሥት ያድኑናል ብለን ተስፋ ያደረግንባቸውና ወደ እነርሱ የተጠጋንባቸው አገሮች ምን እንደ ደረሰባቸው ተመልከቱ! እኛማ እንዴት እናመልጣለን?’ ” ይላሉ። |