ኢሳይያስ 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር ሶርያንና እስራኤልን እንደሚቀጣ 1 ስለ ደማስቆ የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል፦ “እነሆ ደማስቆ ከእንግዲህ ወዲህ ከተማነትዋ ቀርቶ የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤ 2 የሶርያ ከተሞች ሰው የማይኖርባቸው ባድማዎች ይሆናሉ፤ በጎችና ከብቶች በዚያ ይሰማራሉ፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም። 3 እስራኤል ያለ መከላከያ ትቀራለች፤ ደማስቆም ነጻነትዋን ትገፈፋለች፤ ከጥፋት የተረፉ እነዚያ ሶርያውያን እንደ እስራኤል ሕዝብ የተዋረዱ ይሆናሉ፤ እኔ የሠራዊት አምላክ ይህን ተናግሬአለሁ። 4 “በዚያን ቀን የእስራኤል ታላቅነት ይዋረዳል፤ ብልጽግናቸውም ጠፍቶ ይደኸያሉ። 5 እስራኤል እህሉ ታጭዶ መከር ከተሰበሰበ በኋላ ባዶውን እንደሚቀር እርሻ ትሆናለች፤ ከመከር በኋላ የተራቈተ የራፋይምን ሸለቆም ትመስላለች። 6 እስራኤል በላይኛው ቅርንጫፍ ላይ ሁለት ወይም ሦስት ፍሬዎች ብቻ እንዳሉት፥ እንዲሁም በታችኛው ቅርንጫፉ ላይ አራት ወይም አምስት ፍሬዎች እንደ ቀሩበት የወይራ ዛፍ ትሆናለች፤ ሆኖም ጥቂት ሕዝቦች ይተርፋሉ። እኔ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” 7 ያም ቀን ሲደርስ ሕዝቡ ርዳታ ለማግኘት ወደ እስራኤል ቅዱስ ወደ ፈጣሪአቸው ይመለሳሉ፤ 8 ከዚያን በኋላ በገዛ እጃቸው በሠሩት መሠዊያ መታመናቸው ይቀራል፤ እንዲሁም የእጃቸው ሥራ በሆኑት በአሼራ ምስልና ዕጣን ሊያጥኑባቸው በሠሩአቸው መሠዊያዎች መተማመናቸውን ይተዋሉ። 9 በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን አደጋ ባደረሱባቸው ጊዜ የሒዋውያንና የአሞራውያን ከተሞች ባድማ እንደ ሆኑት የእናንተም ጠንካራ ከተሞች ባድማዎች ይሆናሉ። 10 እስራኤል ሆይ እናንተ እንደ ጽኑ አለት መከላከያ ሆኖ የተቤዣችሁን እግዚአብሔርን ረስታችኋል፤ ስለዚህ ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ድንቅና ብርቅ የሆነ ተክል ብትተክሉና 11 በዚያው በተከላችሁት ቀን አድጎ ቢያብብ እንኳ ከቶ አታመርቱትም፤ በዚህ ፈንታ የምታመርቱት ችግርና የማይፈወስ በሽታ ይሆናል። እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንደሚከላከል 12 እንደ ባሕር ሞገድ ድምፀ ለሚያሰሙ ለብዙ ወገን ስብስቦች ወዮላቸው! እንደ ኀይለኛ ጐርፍ ለሚጣደፉ ሕዝቦች ወዮላቸው! 13 ሕዝቦች እንደ ኀይለኛ ውሃ ድምፅ ያሰማሉ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሲገሥጻቸው በተራራ ላይ ገለባዎች በነፋስ እንደሚበተኑና በዐውሎ ነፋስም ዐቧራ እንደሚበተን ርቀው ይሸሻሉ። 14 በምሽት ጊዜ እነሆ፥ ሽብር ይሆናል፤ በማለዳ ግን ይጠፋሉ፤ የሚዘርፉንና የሚበዘብዙን ሰዎችም ዕድል ፈንታ ይኸው ነው። |