ኢሳይያስ 15 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበሞአብ ላይ የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል 1 ስለ ሞአብም የተነገረው ቃል ይህ ነው፤ የዔርና ቂር ከተሞች በአንድ ቀን ሌሊት ተደመሰሱ፥ የሞአብ ምድር ጭር አለች፤ 2 የጺቦን ሕዝብም በቤተ ጣዖታቸው ለማልቀስ ወደ ኰረብታ ይወጣሉ፤ የሞአብ ሕዝብ ስለ ነቦና ስለ ሜዳባ ከተሞቻቸው በከባድ ሐዘን ያለቅሳሉ፤ ከሐዘናቸውም የተነሣ ጠጒራቸውንና ጢማቸውን ተላጭተዋል። 3 በየመንገዱ የሚታዩት ማቅ ለብሰው ነው፤ በሰገነቶቻቸውና በአደባባዮቻቸው ሁሉም እንባቸውን እያፈሰሱ ያለቅሳሉ። 4 የሐሴቦንና የኤልዓሌ ሕዝቦች ይጮኻሉ፤ የጩኸታቸውም ድምፅ እስከ ያሐጽ ድረስ ይሰማል፥ የሞአብ ወታደሮች ሳይቀሩ ወኔያቸው ከድቶአቸው በፍርሃት ተርበደበዱ። 5 ስለ ሞአብ ከልቤ አለቅሳለሁ፤ ሕዝቡ ወደ ጾዓርና ወደ ዔግላት ሸሊሺያ ኰበለሉ፤ ጥቂቶችም ወደ ሉሒት አቀበት ወጡ፤ በሚወጡበትም ጊዜ ያለቅሱ ነበር፤ ሌሎች ደግሞ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ስለ ጥፋታቸው እያለቀሱ ወደ ሖሮናይም ለማምለጥ ይሞክራሉ። 6 የኒምሪም ወንዞች ደርቀዋል፤ ምንም ልምላሜ ሳይቀር በአጠገቡ ያለው ሣር ደርቆአል። 7 ሕዝቡ የሰበሰቡትን ሀብት እንደ ያዙ የአኻያ ዛፍ የበቀለበትን ሸለቆ ተሻግረው ይሄዳሉ፤ 8 በሞአብ ጠረፎች በየስፍራው ጩኸት ይሰማል፤ ጩኸቱም እስከ ኤግላይምና እስከ ብኤርኤሊም ደርሶአል። 9 በዲቦን ከተማ የሚገኘው ወንዝ በደም የተሞላ ነው፤ ሆኖም በዲቦን ላይ እግዚአብሔር ከዚያ የባሰ ነገር ያመጣል፤ ከሞአብ ሸሽተው የሚያመልጡትንና እዚያም ከሞት የተረፉትን ሁሉ አንበሳ ልኮ ያጠፋቸዋል። |