Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔር ባቢሎንን እንደሚቀጣ

1 የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እግዚአብሔር ገልጦለት ስለ ባቢሎን የተናገረው የትንቢት ቃል ይህ ነው፤

2 ምንም ነገር በማይበቅልበት ተራራ ጫፍ ሆናችሁ ምልክት ስጡ፤ ወደ ትዕቢተኞቹ የባቢሎን ገዢዎች ወደሚያስገባው በር እንዲገቡ ትእዛዝ ስጡ።

3 ቊጣዬን ተግባራዊ ያደርጉ ዘንድ ቅዱሳኔን አዝዤአለሁ፤ ድሌ የሚያስደስታቸውን ኀያላኔን ጠርቼአለሁ።

4 በተራሮች ላይ የሚሰማውን ጩኸት አድምጡ፤ ይህም ጩኸት በአንድነት የተሰበሰቡ የብዙ ሕዝብ መንግሥታት ሁካታ ነው፤ የሠራዊት አምላክ ሠራዊቱን ለጦርነት እያዘጋጀ ነው፤

5 እነርሱም በምድር ዳርቻ ከሚገኙ ከሩቅ አገሮች የመጡ ናቸው፤ እግዚአብሔር አገሪቱን በሞላ ለማጥፋት የቊጣ መሣሪያ የሆነ ሠራዊቱን አሰልፎአል።

6 ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ጥፋትን የሚያመጣበት ቀን ስለ ተቃረበ “ዋይ! ዋይ!” እያላችሁ አልቅሱ።

7 ከፍርሃት የተነሣ የእያንዳንዱ ሰው እጅ ይዝላል፤ የእያንዳንዱም ሰው ልብ በፍርሃት ይዋጣል፥

8 የምትወልድ ሴት በምጥ እንደምትሠቃይ እነርሱም በፍርሃት ይሠቃያሉ፤ እርስ በርሳቸው በፍርሃት ይተያያሉ።

9 እነሆ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቊጣና መዓት የሚፈጸምበት ያ ቀን እጅግ አስፈሪ ነው፤ በዚያን ጊዜ በእርስዋ የሚኖረው ኃጢአተኛ ሕዝብ ስለሚደመሰስ ምድሪቱ ባድማ ትሆናለች።

10 እያንዳንዱ ኮከብና የከዋክብት ክምችቱ ብርሃን መስጠቱን ያቆማል፤ የንጋት ፀሐይ ገና ከመውጣትዋ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም።

11 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ዓለምን ስለ ክፋቱ፥ ክፉዎችን ስለ ኃጢአታቸው እቀጣለሁ፤ የኲራተኞችን ማን አለብኝነት አዋርዳለሁ፤ የትዕቢተኛውንም ጭካኔ አጠፋለሁ።

12 ሰውን ከወርቅ ይልቅ፥ ከኦፌር ወርቅም የበለጠ ብርቅና ውድ አደርገዋለሁ።

13 እኔ የሠራዊት አምላክ ቊጣዬን በምገልጥበት ጊዜ ሰማይን አንቀጠቅጣለሁ፤ ምድርም ከስፍራዋ እንድትናወጥ አደርጋለሁ።

14 “አዳኝ እንዳባረረው አጋዘንና ጠባቂ እንደሌለው የበግ መንጋ ይባዝን የነበረው እያንዳንዱ ሰው ወደ ወገኖቹ ይመለሳል፤ ወደ አገሩም ይሸሻል።

15 የተያዘም ሁሉ በሰይፍ ይገደላል።

16 ሕፃኖቻቸው በፊታቸው ተጨፍጭፈው ይሞታሉ፤ ቤቶቻቸው ይዘረፋሉ፤ ሚስቶቻቸው ይደፈራሉ።”

17 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሜዶናውያንን በባቢሎናውያን ላይ አስነሣለሁ፤ እነርሱ ለብር ደንታ የላቸውም፤ በወርቅም አይደለሉም።

18 በቀስታቸውና በፍላጻቸው ወጣቶችን ይገድላሉ፤ ሕፃናትን እንኳ አይምሩም፤ ለልጆችም ርኅራኄ የላቸውም።

19 የባቢሎን መንግሥት ከመንግሥታት ሁሉ እጅግ የተዋበች ናት፤ ለሕዝብዋም መመኪያ ናት፤ ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር ባቢሎንን እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ እገለብጣታለሁ!

20 ዳግመኛ የሚኖርባትም አይገኝም፤ የበረሓ ዘላኖች የሆኑ ዐረቦችም ድንኳን አይተክሉባትም፤ እረኞችም መንጋ አያሰማሩባትም።

21 የምድረ በዳ አራዊት መፈንጫ ትሆናለች ጒጒቶችም ጎጆ ይሠሩባታል፤ ሰጎኖች በዚያ ይኖራሉ፤ ፍርስራሽዋንም የበረሓ ፍየሎች ይዛለሉበታል።

22 በታላላቅ ሕንጻዎችዋና በቤተ መንግሥትዋ ውስጥ የጅቦችና የተኲላዎች ጩኸት ያስተጋባል፤ እነሆ በዚህ ዐይነት ባቢሎን የምትጠፋበት ጊዜ ደርሶአል።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告