Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዕብራውያን 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 እያንዳንዱ የካህናት አለቃ ከሰዎች መካከል ተመርጦ ከእግዚአብሔር ጋር በሚያገናኛቸው ጉዳይ በሰዎች ፋንታ ሆኖ መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ ይሾማል።

2 እርሱ ራሱ ድካም ያለበት ስለ ሆነ አላዋቂዎችንና ስሕተተኞችን በርኅራኄ ሊመለከታቸው ይችላል።

3 እርሱ ራሱም በደካማነቱ ምክንያት የኃጢአት ይቅርታን የሚያስገኝ መሥዋዕትን ማቅረብ የሚገባው ለሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ለራሱም ጭምር ነው።

4 እንደ አሮን በእግዚአብሔር የተጠራ ካልሆነ በቀር ማንም ይህን ክብር በገዛ ራሱ አያገኝም።

5 እንዲሁም ክርስቶስ የካህናት አለቃ የመሆንን ክብር በገዛ ራሱ አልወሰደም፤ ነገር ግን እርሱ የካህናት አለቃ የመሆንን ክብር ያገኘው፥ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ” ካለው ከእግዚአብሔር ነው።

6 በሌላም ስፍራ እግዚአብሔር፥ “እንደ መልከጼዴቅ የክህነት ሹመት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” ይላል።

7 ኢየሱስ ሰው ሆኖ በዚህ ምድር በኖረበት ጊዜ ከሞት ሊያድነው ወደሚችል አምላክ በታላቅ ጩኸትና በብዙ እንባ ጸሎትንና ልመናን አቀረበ፤ በትሕትና ራሱን ታዛዥ በማድረጉ እግዚአብሔር ጸሎቱን ሰማው።

8 የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም እንኳ በተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ።

9 ፍጹም ሆኖ ከተገኘም በኋላ ለሚታዘዙት ሁሉ ለዘለዓለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው።

10 ይህም እግዚአብሔር በመልከ ጼዴቅ የክህነት ሹመት ዐይነት የካህናት አለቃ አድርጎ ሾመው።


ሰዎች እምነታቸውን እንዳይተዉ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

11 ስለዚህ ጉዳይ የምንናገረው ብዙ ነገር አለ፤ ነገር ግን የማስተዋል ችሎታችሁ አነስተኛ ስለ ሆነ ለማስረዳት አስቸጋሪ ነው።

12 እስከ አሁን በነበረው ጊዜ እናንተ አስተማሪዎች መሆን በተገባችሁ ነበር፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል የመጀመሪያውን ትምህርት ሌላ ሰው እንደገና እንዲያስተምራችሁ ያስፈልጋል፤ በዚህ ዐይነት የሚያስፈልጋችሁ ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም።

13 ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ መልካም ነገርን ከክፉ የመለየት ትምህርት አልተለማመደም።

14 ጠንካራ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ግን መልካሙንና ክፉውን የመለየት ልምድ ያላቸው ትላልቅ ሰዎች ናቸው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告