ዕብራውያን 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔርን የሚያስደስት አገልግሎት 1 ሁልጊዜ የእርስ በርስ የወንድማማችነት ፍቅር ይኑራችሁ፤ 2 እንግዳ ተቀብሎ ማስተናገድን አትርሱ፤ እንደዚህ እንግዶችን እየተቀበሉ በማስተናገድ አንዳንድ ሰዎች ሳያውቁ መላእክትን ተቀብለው አስተናግደዋል። 3 ከእነርሱ ጋር አብራችሁ እንደ ታሰራችሁ ያኽል ሆናችሁ እስረኞችን አስታውሱ፤ እናንተም እንደ እነርሱ መከራ የምትቀበሉ ያኽል ሆናችሁ መከራ የሚቀበሉትን አስቡ። 4 ጋብቻ በሁሉ ዘንድ የተከበረ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን እግዚአብሔር ስለሚፈርድባቸው ባልና ሚስት ታማኝነትን በማጒደል ጋብቻን አያርክሱ። 5 ከገንዘብ ፍቅር ራቁ፤ ያላችሁ ይብቃችሁ፤ እግዚአብሔር “ከቶ አልጥልህም፤ ፈጽሞም አልተውህም” ብሎአል። 6 ስለዚህ በመተማመን፥ “ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንላለን። 7 የእግዚአብሔርን ቃል በመጀመሪያ የነገሩአችሁን መሪዎቻችሁን አትርሱ፤ የአኗኗራቸውንና የሥራቸውን ውጤት በማስታወስ እምነታቸውን ተከተሉ። 8 ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትም ዛሬም ለዘለዓለምም ያው ነው፤ አይለወጥም። 9 ባልተለመደ በልዩ ልዩ ዐይነት ትምህርት አትማረኩ፤ ልባችን የመብል ሥነ ሥርዓቶችን በመጠበቅ ሳይሆን በጸጋ ቢጸና መልካም ነው፤ ይህን የምግብ ሥነ ሥርዓት የተከተሉ ሰዎች ምንም አልተጠቀሙም። 10 እኛ መሠዊያ አለን፤ ሆኖም በድንኳኒቱ ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናት በዚህ መሠዊያ ላይ ካለው ምግብ ወስደው መብላት አይፈቀድላቸውም። 11 የአይሁድ የካህናት አለቃ የኃጢአት ይቅርታን የሚያስገኘውን የእንስሳት ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባል፤ የእንስሳቱ በድን ግን ከሰፈሩ ውጪ ይቃጠላል፤ 12 እንዲሁም ኢየሱስ ሕዝቡን በገዛ ራሱ ደም ለመቀደስ ከከተማው በር ውጪ መከራን ተቀበለ። 13 እኛም ከሰፈር ወጥተን ወደ እርሱ እንሂድ፤ የውርደቱም ተካፋዮች እንሁን። 14 እኛ ገና የምትመጣውን ከተማ እንጠባበቃለን እንጂ ጸንታ የምትኖር ከተማ በዚህ ምድር የለችንም። 15 እንግዲህ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የምስጋና መሥዋዕት ዘወትር ለእግዚአብሔር እናቅርብ፤ ይህም ስለ ስሙ በሚመሰክሩት ከንፈሮች የሚቀርብ የምስጋና መሥዋዕት ነው። 16 መልካም ነገር ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ፤ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ እንዲህ ያለው መሥዋዕት ነው። 17 ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ በሥልጣናቸውም ሥር ሁኑ፤ እነርሱ የሚጠየቁበት ኀላፊነት ስላለባቸው ስለ ነፍሳችሁ ጉዳይ ይተጋሉ፤ እናንተ ብትታዘዙአቸው እነርሱ ሥራቸውን በደስታ ያከናውናሉ፤ ያለበለዚያ ሥራቸውን በሐዘን ይሠራሉ፤ ይህም እናንተን የሚጠቅም አይሆንም። 18 ጸልዩልን፤ ንጹሕ ኅሊና እንዳለን እርግጠኞች ነን፤ በሁሉም መንገድ በመልካም ጠባይ ለመኖር እንመኛለን፤ 19 ይልቁንም ተግታችሁ እንድትጸልዩ አጥብቄ የምለምናችሁ በፍጥነት ወደ እናንተ እንድመለስ ነው። የመደምደሚያ ጸሎት 20 ታላቁን የበጎች እረኛ ጌታችንን ኢየሱስን በዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ደም ከሞት ያስነሣው የሰላም አምላክ 21 ፈቃዱን ለመፈጸም እንድትበቁ በመልካም ነገር ሁሉ ያስታጥቃችሁ፤ ደስ የሚያሰኘውንም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ያድርግ፤ ለኢየሱስ ክርስቶስም ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን። ማጠቃለያ 22 ወንድሞች ሆይ! ይህ የጻፍኩላችሁ መልእክት አጭር ስለ ሆነ ይህን የምክር ቃሌን በትዕግሥት እንድትቀበሉ አጥብቄ እለምናችኋለሁ። 23 ወንድማችን ጢሞቴዎስ ከእስር ቤት እንደ ወጣ እንድታውቁ እወዳለሁ፤ በቶሎ ወደዚህ ከመጣ ከእርሱ ጋር ወደ እናንተ መጥቼ አያችኋለሁ። 24 ለመሪዎቻችሁና ለቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ ከኢጣልያ መጥተው እዚህ ያሉት ክርስቲያኖች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 25 ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን። |