ዕብራውያን 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር አባታችን ስለ መሆኑ 1 እንደ ደመና በዙሪያችን የከበቡን እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ስላሉን እኛ እንደ ሸክም የሆነብንን ነገር ሁሉ በእኛ ላይ የተጣበቀብንን ኃጢአት አስወግደን በፊታችንም ያለውን የሩጫ እሽቅድድም በትዕግሥት በመጽናት እንሩጥ። 2 የምንሮጠውም የእምነታችን መሥራችና ፈጻሚ የሆነውን ኢየሱስን በመመልከት ነው፤ እርሱ በፊቱ በተደቀነው ደስታ ምክንያት በመስቀል ላይ የመሞትን ውርደት ከምንም ሳይቈጥር የመስቀልን መከራና ሞት ታገሠ፤ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝም ተቀመጠ። 3 እንግዲህ ሳትሰለቹና ተስፋ ሳትቈርጡ ይህን ሁሉ የኃጢአተኞችን ተቃውሞ የታገሠውን ኢየሱስን ተመልከቱ። 4 እናንተ ከኃጢአት ጋር በመታገል ገና ደም እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም። 5 እግዚአብሔር እንደ ልጆቹ አድርጎ እንዲህ ሲል የመከራችሁን ረስታችኋል፤ “ልጄ ሆይ! የጌታን ተግሣጽ አታቃል፤ በቀጣህም ጊዜ ተስፋ አትቊረጥ፤ 6 ጌታ የሚወደውን ይገሥጻል፤ እንደ ልጁ አድርጎ የሚያየውንም ይቀጣል።” 7 እግዚአብሔር እንደ ልጆቹ ስለሚቈጥራችሁ ቅጣትን ታገሡ፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? 8 ልጆች የሆኑ ሁሉ የሚቀበሉትን ቅጣት እናንተም ካልተቀበላችሁ ዲቃሎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። 9 ከዚህም በቀር እኛ ሁላችን የሚቀጡን የሥጋ አባቶች ነበሩን፤ እናከብራቸውም ነበር፤ ታዲያ፥ በሕይወት ለመኖር ለመንፈሳዊ አባታችን በይበልጥ መታዘዝ እንዴት አይገባንም! 10 እነርሱ መልካም መስሎ እንደ ታያቸው ለጥቂት ጊዜ ቀጥተውናል፤ እርሱ ግን የቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለጥቅማችን ይቀጣናል። 11 ቅጣት ሁሉ በወቅቱ የሚያሳዝን እንጂ የሚያስደስት አይመስልም፤ በኋላ ግን ለተለማመዱት ሰዎች ሰላም የሞላበትን የጽድቅ ፍሬ ያስገኝላቸዋል። ምክርና ማስጠንቀቂያ 12 ስለዚህ የዛሉትን እጆቻችሁንና የደከሙትን ጒልበቶቻችሁን አበርቱ። 13 አንካሳ የሆነው እንዲፈወስ እንጂ ከቦታው ወጥቶ እንዳይናጋ ለእግራችሁ የቀና መንገድ አድርጉ። 14 ያለ ቅድስና ማንም ጌታን ማየት ስለማይችል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ፤ በቅድስናም ለመኖር ትጉ፤ 15 ከእናንተ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጐድልበት ተጠንቀቁ፤ እንዲሁም ምንም መራራ ፍሬ የሚያፈራ ሥር በመካከላችሁ እንዳይበቅልና እንዳያስቸግራችሁ ብዙዎችንም እንዳያረክስ ተጠንቀቁ። 16 ሴሰኛ የሆነ ወይም ለአንድ ጊዜ ምግብ ብሎ ብኲርናውን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ነውረኛ የሆነ ሰው እንዳይገኝ ተጠንቀቁ። 17 በኋላም ዔሳው በረከትን እንደገና ለመቀበል በፈለገ ጊዜ ይህን በረከት እንደ ተከለከለ ታውቃላችሁ፤ እያለቀሰ እንኳ ያንን በረከት ተግቶ ቢፈልግ ሊያገኘው አልቻለም። ለንስሓ ምንም ዕድል አላገኘም። 18 እናንተ በእጅ ወደሚዳሰሰው ወይም ወደሚቃጠለው ወደ ሲና ተራራ አልደረሳችሁም፤ ወደ ጭጋጉ፥ ወደ ጨለማውም፥ ወደ ዐውሎ ነፋሱም፥ 19 የእምቢልታ ድምፅ ወይም የሚነገረው ቃል ወደሚሰማበትም አልደረሳችሁም፤ ያንን ቃል የሰሙ ሰዎች “ከእንግዲህ ወዲህ ሌላ ቃል አይነገረን” በማለት እስከ መለመን ደርሰዋል። 20 “እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ በድንጋይ ተወግሮ ይሙት” የሚለው ትእዛዝ ስለ ከበደባቸው ሊሸከሙት አልቻሉም። 21 የታየው ድርጊት እጅግ አስፈሪ ከመሆኑ የተነሣ ሙሴ እንኳ “እኔ ፈራሁ፤ ተንቀጠቀጥኩም” አለ። 22 እናንተ ግን ወደ ጽዮን ተራራ ቀርባችኋል፤ እርስዋ የሕያው እግዚአብሔር ከተማ የሆነችው ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ናት፤ በደስታ ወደተሰበሰቡት፥ በብዙ ሺህ ወደሚቈጠሩት መላእክት ቀርባችኋል። 23 ስማቸው በሰማይ ወደተጻፈው፥ የቤተ ክርስቲያን የበኲር ልጆች ወደሆኑት ወደ አማኞች ጉባኤ፥ የሁሉ ፈራጅ ወደ ሆነው አምላክና ፍጹምነትን ወዳገኙት የጻድቃን ነፍሳት ቀርባችኋል። 24 የአዲስ ኪዳን ማእከላዊ አስማሚ ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤል ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገረውና ወደተረጨው ደሙም ቀርባችኋል። 25 ያንን የሚናገረውን አንቀበልም እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ እነዚያ እግዚአብሔር በሰው አማካይነት ከምድር ሲናገራቸው አንሰማም ያሉት ካላመለጡ፥ ታዲያ እኛ ከሰማይ የሚናገረንን ባንቀበል እንዴት እናመልጣለን! 26 በዚያን ጊዜ ቃሉ ምድርን አናውጦአል፤ አሁን ግን “ምድርን ብቻ ሳይሆን አንድ ጊዜ ደግሜ ሰማይን ጭምር አናውጣለሁ” በማለት ቃል ገብቶአል። 27 ይህ “አንድ ጊዜ ደግሜ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የማይናወጡ ነገሮች ጸንተው እንዲኖሩ የሚናወጡ ወይም የተፈጠሩ ነገሮች መወገዳቸውን ነው። 28 እንግዲህ እኛ የማትናወጠውን መንግሥት ስለምንወርስ እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ደስ በሚሰኝበት ሁኔታም በአክብሮትና በፍርሃት እናገልግለው። 29 አምላካችን እንደሚያቃጥል እሳት ነው። |