Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዕብራውያን 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እምነት

1 እምነት ማለት በተስፋ የሚጠበቀውን ነገር “አዎን በእውነት ይሆናል” ብሎ መቀበል ነው፤ በዐይን የማይታየውንም ነገር እንደሚታይ አድርጎ መቊጠር ነው።

2 የቀድሞ ሰዎች የተመሰገኑት በእምነት ምክንያት ነው።

3 ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተፈጠረ የምንረዳው በእምነት ነው። ስለዚህ የሚታየው ነገር ሁሉ ከማይታየው እንደ ተሠራ እናውቃለን።

4 አቤል ከቃየል መሥዋዕት የበለጠውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀረበው በእምነት ነው፤ እግዚአብሔር የአቤልን መባ በደስታ በተቀበለ ጊዜ አቤል በእምነቱ ጻድቅ መሆኑ ተመሰከረለት፤ አቤል ቢሞትም እንኳ በእምነቱ አማካይነት አሁንም እየተናገረ ነው።

5 ሔኖክ ሞት እንዳይደርስበት ወደ ላይ የተወሰደው በእምነት ነው፤ እግዚአብሔር ስለ ወሰደውም አልተገኘም፤ ከመወሰዱ በፊት ደግሞ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታል።

6 ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሰው እግዚአብሔር መኖሩንና እርሱን ለሚፈልጉት ሰዎችም ስጦታን የሚሰጥ መሆኑን ማመን አለበት።

7 ገና በዐይን ስለማይታዩት ነገሮች እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ጊዜ ኖኅ እግዚአብሔርን በመፍራት ቤተሰቡን ለማዳን መርከብን የሠራው በእምነት ነው፤ በኖኅም እምነት ዓለም ኃጢአተኛ መሆኑ ታውቆ ተፈረደበት፤ ኖኅም በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ ወረሰ።

8 አብርሃም ወጥቶ ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ እንዲሄድ በተጠራ ጊዜ ምንም እንኳ ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም ለመሄድ የታዘዘው በእምነት ነው።

9 ከእርሱ ጋር የተስፋው ቃል ወራሾች ከሆኑት ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር በተስፋይቱ አገር መጻተኛ ሆኖ በድንኳን የኖረው በእምነት ነው።

10 ይህንንም ያደረገው ጽኑ መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር ያቀዳትንና የሠራትን ከተማ ይጠባበቅ ስለ ነበር ነው።

11 ሣራም ተስፋ የሰጣት እግዚአብሔር ታማኝ መሆኑን ስላወቀች ምንም እንኳ በዕድሜ በመግፋቷ መውለድ የማትችል ብትሆን የመፅነስን ኀይል ያገኘችው በእምነት ነው።

12 ስለዚህ እንደ ሞተ ሰው ከሚቈጠረው ከአንዱ ከአብርሃም እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛና እንደ ባሕር ዳር አሸዋ የማይቈጠር ዘር ተገኘ።

13 እነዚህ ሁሉ በእምነት እንዳሉ ሞቱ፤ እግዚአብሔር ሊሰጣቸው ቃል የገባላቸውንም ነገር አላገኙም፤ ነገር ግን ከሩቅ አይተው ልክ እንዳገኙት አድርገው በደስታ ተቀበሉት። በምድር ላይ እንግዶችና መጻተኞች መሆናቸውንም ተገነዘቡ።

14 እንዲህ የሚናገሩ ሰዎች የራሳቸው የሚሆነውን አገር እንደሚጠባበቁ በግልጽ ያመለክታሉ።

15 ያንን የወጡበትን አገር አስታውሰውት ቢሆኑ ኖሮ ወደዚያ ለመመለስ በቻሉ ነበር።

16 አሁን ግን የሚበልጠውን፥ በሰማይ ያለውን አገር ይናፍቃሉ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ከተማን ስላዘጋጀላቸው “አምላካችን” ብለው ቢጠሩት አያሳፍረውም።

17 አብርሃም በተፈተነበት ጊዜ ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው በእምነት ነው፤ ያ የተስፋ ቃል የተቀበለው አብርሃም አንድ ልጁን ሊሠዋው ነበር፤

18 ታዲያ፥ እግዚአብሔር፥ “በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል” ብሎት ነበር።

19 እግዚአብሔር ከሞት የማስነሣት ችሎታ እንዳለው አብርሃም በማመኑ ልክ ከሞት እንደ ተነሣ ያኽል ይስሐቅን እንደገና አገኘው።

20 ይስሐቅ ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር በማሰብ ያዕቆብንና ዔሳውን የባረካቸው በእምነት ነው።

21 ያዕቆብ የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን የባረካቸውና በብትሩ ጫፍ ተደግፎ የሰገደው በእምነት ነው።

22 ዮሴፍም የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ እስራኤላውያን ከግብጽ እንደሚወጡ የተናገረው ስለ ዐፅሙም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ትእዛዝ የሰጠው በእምነት ነው።

23 የሙሴ ወላጆች ሙሴ በተወለደ ጊዜ መልከ መልካም መሆኑን ስላዩ የንጉሡን ትእዛዝ ሳይፈሩ ሦስት ወር የሸሸጉት በእምነት ነው።

24 ሙሴም ካደገ በኋላ “የፈርዖን የልጅ ልጅ” ተብሎ መጠራትን ያልፈቀደው በእምነት ነው፤

25 ስለዚህም እርሱ በኃጢአት ከሚገኘው ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ።

26 ወደፊትም የሚቀበለውን ዋጋ ስለ ተመለከተ ከግብጽ ሀብት ይልቅ ስለ መሲሑ መዋረድ የበለጠ መሆኑን አሰበ።

27 የንጉሡንም ቊጣ ሳይፈራ ከግብጽ የወጣው በእምነት ነው፤ በዐይን የማይታየውንም አምላክ እንዳየው ያኽል ሆኖ በዓላማው ጸና።

28 የበኲር ልጆችን ለመግደል የታዘዘው መልአክ የእስራኤላውያንን የበኲር ልጆች እንዳይገድል በማለት ሙሴ የፋሲካና የደም መርጨትን ሥርዓት ያደረገው በእምነት ነው።

29 እስራኤላውያን በደረቅ ምድር እንደሚሻገሩ ሆነው ቀይ ባሕርን የተሻገሩት በእምነት ነው፤ ግብጻውያን ግን እንዲሁ ለማድረግ በሞከሩ ጊዜ ሁሉም ሰጠሙ።

30 እስራኤላውያን በኢያሪኮ ቅጽሮች ዙሪያ ሰባት ቀን ከዞሩ በኋላ ቅጽሮቹን ያፈረሱት በእምነት ነው።

31 አመንዝራይቱ ረዓብ ሰላዮችን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙት ጋር ከመሞት የተረፈችው በእምነት ነው።

32 እንግዲህ ሌላ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎን፥ ስለ ባራቅ፥ ስለ ሶምሶን፥ ስለ ዮፍታሔ፥ ስለ ዳዊት፥ ስለ ሳሙኤል፥ ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥረኛል፤

33 እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፤ በፍትሕ አስተዳደሩ፤ የተሰጣቸውንም ተስፋ አገኙ፤ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፤

34 የእሳትን ኀይል አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከደካማነት ወደ ብርቱነት ተለወጡ፤ በጦርነት ኀይለኞች ሆኑ፤ የወራሪ ጠላትን ወታደሮች አባረሩ፤

35 ሴቶች የሞቱባቸውን ዘመዶቻቸውን ከሞት ተነሥተው አገኘአቸው። ሌሎችም የበለጠ ትንሣኤ ለማግኘት አስበው ልዩ ልዩ ሥቃይ ተቀበሉ፤ ከእስራት ነጻ መሆንንም አልፈቀዱም።

36 ሌሎች መዘባበቻ ሆነው ተገረፉ፤ ሌሎች በእግር ብረት ታስረው ወደ ወህኒ ቤት ተጣሉ፤

37 በድንጋይ ተወገሩ፤ በመጋዝ ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተገደሉ፤ የበግና የፍየል ቆዳ ለብሰው ተንከራተቱ፤ ድኾችና ስደተኞች ሆነው ተንገላቱ፤

38 በበረሓ፥ በተራራ፥ በምድር ውስጥ ባሉ ዋሻዎችና ፈፋዎች ዞሩ። በዚህም ዐይነት ዓለም ለእነርሱ ተገቢ ስፍራ ሆና አልተገኘችም።

39 እነዚህ ሁሉ ስለ እምነታቸው የተመሰከረላቸው ቢሆኑም የተሰጣቸውን ተስፋ ገና አላገኙም።

40 እግዚአብሔር ለእኛ የተሻለ ነገር ዐቅዶአልና፤ ስለዚህ እነርሱ ከእኛ ጋር እንጂ ብቻቸውን ፍጹሞች መሆን አይችሉም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告