Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዕንባቆም 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 እግዚአብሔር ለነቢዩ ለዕንባቆም በራእይ የገለጠለት ቃል የሚከተለው ነው፦


ዕንባቆም ስለ ፍትሕ መጓደል የተሰማው ሐዘን

2 እግዚአብሔር ሆይ! ርዳታህን በመጠየቅና በእኛ ላይ የደረሰውን ዐመፅ በመግለጥ ወደ አንተ ስንጮህ የምታዳምጠንና የምታድነን መቼ ነው?

3 ለምን ይህ ሁሉ ግፍ ሲደርስ እንዳይ አደረግኸኝ? አንተስ ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈጸም እንዴት ዝም ብለህ ትመለከታለህ? ጥፋትንና ዐመፅን አያለሁ፤ ጠብና ክርክርም ይነሣሉ።

4 በዚህ መሠረት ሕግ ላልቶአል፤ ፍትሕም ተዛብቶአል፤ ክፉዎች በደጋግ ሰዎች ላይ ከበባ አድርገዋል፤ ስለዚህ ፍርድ ተጣሟል።


ከእግዚአብሔር የተሰጠ መልስ

5 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ አለ፦ “በዙሪያችሁ ያሉትን ሕዝቦች እስቲ ተመልከቱ፤ በምታዩት ሁሉ እጅግ ተደነቁ፤ ማንም ሰው ቢነግራችሁ እንኳ ልታምኑ የማትችሉትን አስደናቂ ነገር በዘመናችሁ እሠራለሁ።

6 እነሆ እነዚያን ጨካኞችና ችኲሎች ባቢሎናውያንን አስነሣባችኋለሁ፤ እነርሱ የራሳቸው ያልሆነውን ምድር ሁሉ በጦር ኀይል ለመያዝ በየሀገሩ ይዞራሉ።

7 እነርሱ አስፈሪና አስደንጋጭ ናቸው፥ የራሳቸውን ክብር ማስጠበቂያ ሕግ ያወጣሉ።

8 “ፈረሶቻቸው ከነብር ይበልጥ ፈጣኖች፥ ከማታ ተኲላ ይልቅ አስፈሪዎች ናቸው፤ ፈረሰኞቻቸውም እየጋለቡ ከሩቅ ይመጣሉ፤ ነጥቀው ለመብላትም እንደ ንስር ይበራሉ።

9 “ሠራዊታቸው ሁሉ የዐመፅ ሥራ ለመፈጸም ይገሠግሣሉ፤ ፊታቸው ከወደ ምሥራቅ እንደሚመጣ ነፋስ ያቃጥላል፤ ምርኮኞችንም እንደ አሸዋ ይሰበስባሉ።

10 በነገሥታት ላይ ይሳለቃሉ፤ መሪዎቻቸውንም ይንቃሉ፤ በምሽጎቹ ሁሉ ላይ በመሳቅ ዐፈር ቈልለው ይይዙዋቸዋል።

11 ከዚህ በኋላ እንደ ነፋስ ጠራርገው ይሄዳሉ፤ እነዚህ ጒልበታቸውን እንደ አምላካቸው የሚቈጥሩ ሰዎች በደለኞች ናቸው።”


ዕንባቆም ስለ ፍትሕ መጓደል ዳግመኛ የተሰማው ሐዘን

12 እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! አንተ ከጥንት ጀምሮ የነበርክ ቅዱስ ነህ፤ አንተ ስለምትጠብቀን አንሞትም፥ እነርሱ ፍርድህን ተግባራዊ እንዲያደርጉ መድበሃቸዋል፤ አምባችን ሆይ! እኛን እንዲቀጡ ለእነርሱ ሥልጣን ሰጥተሃቸዋል።

13 ዐይኖችህ እጅግ የጠሩ ስለ ሆኑ፥ ክፉ ነገርን መመልከት አይሆንላቸውም፤ አንተም ክፉ ነገር ሲሠራ ማየት አይስማማህም፤ ታዲያ እነዚህን ዐመፀኞችን እንዴት ዝም ብለህ ትመለከታቸዋለህ? ክፉዎችስ ከእነርሱ ይበልጥ ደጋግ የሆኑ ሰዎችን ሊያጠፉ ሲነሡ ስለምን ዝም ትላለህ?

14 ሰዎችን እንደ ባሕር ዓሣዎችና መሪ እንደሌላቸው በደረታቸው እየተሳቡ እንደሚሄዱ ፍጥረቶች የምታደርጋቸው ለምንድን ነው?

15 ዓሣ በመንጠቆ እንደሚያዝ ጠላት ሁሉንም ይይዛቸዋል፤ በመረብም እንደሚጐተት ይጐትታቸዋል፤ በማከማቻው ይሰበስባቸዋል፤ ይህን በማድረጉ በደስታ ይፈነጥዛል።

16 በምግብ ስለሚያበለጽጉትና በቅንጦት እንዲኖር ስለሚያደርጉት ለመረቡ መሥዋዕት ያቀርባል፤ ለማከማቻውም ዕጣን ያጥናል።

17 ታዲያ እርሱ መረቡን እያራገፈና ያለምሕረት ሕዝቦችን እየፈጀ መቀጠል አለበትን?

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告