Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ገላትያ 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እርስ በርስ መተጋገዝ

1 ወንድሞች ሆይ! ሰው ተሳስቶ አንዳች ጥፋት አድርጎ ቢገኝ መንፈሳውያን የሆናችሁት እናንተ እንዲህ ዐይነቱን ሰው በገርነት አቅኑት፤ ነገር ግን አንተም በዚህ ዐይነት ፈተና እንዳትወድቅ ተጠንቀቅ።

2 ከእናንተ እያንዳንዱ የሌላውን ከባድ ሸክም ይሸከም፤ በዚህ ዐይነት የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ።

3 ማንም ሰው ከሌሎች የሚሻልበት ነገር ሳይኖረው “እኔ ከሌሎች እበልጣለሁ” ብሎ ቢያስብ ራሱን ያታልላል።

4 እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሥራ መርምሮ ይፈትን፤ ከዚህ በኋላ ራሱን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ሳይሆን ለራሱ ብቻ የሚመካበትን ነገር ያገኛል።

5 እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሸክም መሸከም አለበት።

6 ቃሉን የሚማር ሰው ከአስተማሪው ጋር መልካሙን ነገር ሁሉ ይካፈል።

7 ራሳችሁን አታታሉ፤ ሰው የሚያጭደው የዘራውን ስለ ሆነ በእግዚአብሔር ላይ አትቀልዱ፤

8 ሥጋውን ለማስደሰት የሚዘራ ከሥጋው ሞትን ያጭዳል፤ መንፈስን ለማስደሰት የሚዘራ ከመንፈስ የዘለዓለም ሕይወትን ያጭዳል።

9 ተስፋ ካልቈረጥን ወቅቱ ሲደርስ መከር ስለምንሰበስብ መልካም ሥራን ከመሥራት አንስነፍ።

10 ምቹ ጊዜ ካገኘን ለሰዎች ሁሉ ይልቁንም ለሚያምኑ ቤተ ሰዎች መልካም ነገርን እናድርግ።


የመጨረሻ ምክርና ሰላምታ

11 እንዴት ባሉ ታላላቅ ፊደሎች ይህን በእጄ እንደ ጻፍኩላችሁ ተመልከቱ!

12 እንድትገረዙ የሚያስገድዱአችሁ በውጭ መልካም መስለው ለመታየት የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። ይህን የሚያደርጉትም በክርስቶስ መስቀል ምክንያት ስደት እንዳይደርስባቸው ብለው ነው።

13 እነርሱ በእናንተ ሥጋ ለመመካት ብለው እንድትገረዙ ይፈልጋሉ እንጂ የተገረዙትም እንኳ ራሳቸው ሕግን አይፈጽሙም።

14 ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር በሌላ መመካት ከእኔ ይራቅ፤ በዚህም መስቀል ዓለም ከእኔ ተለይቶአል፤ እኔም ከዓለም ተለይቼአለሁ።

15 ስለዚህ መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ምንም አይጠቅምም፤ የሚጠቅመውስ አዲስ ፍጥረት መሆን ነው።

16 ይህን መመሪያ ለሚከተሉ ሁሉና የእግዚአብሔር ወገኖች ለሆኑት እስራኤላውያን ሰላምና ምሕረት ይሁን።

17 በሰውነቴ ላይ ያለው የግርፋት ምልክት የኢየሱስ አገልጋይ መሆኔን ስለሚያመለክት ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ።

18 ወንድሞች ሆይ! የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን! አሜን።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告