ገላትያ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 በሰዎች ወይም በሰው አማካይነት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስና እርሱንም ከሞት ባስነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ ሆኜ ከተላክሁ ከእኔ ከጳውሎስ፥ 2 ከእኔም ጋር ካሉት ወንድሞች ሁሉ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያን የተላከ። 3 ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 4 ከዚህ ከክፉ ዘመን ያድነን ዘንድ በአምላካችንና በአባታችን ፈቃድ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። 5 ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን! አሜን። እውነተኛው ወንጌል አንድ ብቻ ስለ መሆኑ 6 በክርስቶስ ጸጋ ከጠራችሁ አምላክ እንዲህ ፈጥናችሁ መለየታችሁና ወደ ሌላ ወንጌል ማዘንበላችሁ ያስደንቀኛል። 7 ይህንንም ያልኩት ግራ የሚያጋቡአችሁና የክርስቶስንም ወንጌል ለማጣመም የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች ስላሉ ነው እንጂ ወንጌልማ በመሠረቱ አንድ ብቻ ነው። 8 ይሁን እንጂ እኛም ብንሆን፥ ወይም የሰማይ መልአክ እንኳ ቢሆን፥ እኛ ከሰበክንላችሁ የተለየ ሌላ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን! 9 ከዚህ በፊት እንዳልኩት አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ እናንተ ከተቀበላችሁት የተለየ ሌላ ወንጌል ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን! 10 ታዲያ፥ እኔ የምፈልገው ሰው እንዲያመሰግነኝ ነውን? ወይስ እግዚአብሔር እንዲያመሰግነኝ? ወይስ ሰውን ደስ ለማሰኘት የምፈልግ መስሎአችሁ ይሆን? ሰዎችን ለማስደሰት የምፈልግ ብሆን ኖሮ የክርስቶስ አገልጋይ ባልሆንኩም ነበር። የጳውሎስ ለሐዋርያነት መጠራት 11 ወንድሞቼ ሆይ! እኔ የሰበክሁላችሁ ወንጌል ከሰው የተገኘ አለመሆኑን እንድታውቁ እፈልጋለሁ። 12 ይህን ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ገለጠልኝ እንጂ ከማንም ሰው አልተቀበልኩትም፤ ወይም ማንም ሰው አላስተማረኝም። 13 ቀድሞ የአይሁድ እምነት ተከታይ በነበርኩበት ጊዜ እንዴት እንደ ኖርኩ ሰምታችኋል፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ከመጠን በላይ እያሳደድኩ ለማጥፋት እጥር ነበር። 14 የአይሁድን እምነት በመጠበቅ በዘመኔ ከነበሩት ከብዙዎቹ አይሁድ ወገኖቼ ሁሉ እበልጥ ነበር፤ ስለ አባቶችም ወግ ከፍተኛ ቅናት ነበረኝ። 15 ነገር ግን ከመወለዴ በፊት እግዚአብሔር መረጠኝ፤ በጸጋውም ጠራኝ። 16 ለአሕዛብ ስለ ልጁ የምሥራቹን ቃል እንዳበሥር እግዚአብሔር ልጁን ሊገልጥልኝ በወደደ ጊዜ እኔ ከማንም ጋር አልተማከርኩም፤ 17 ወይም ከእኔ በፊት ሐዋርያት የነበሩትን ለመገናኘት ወደ ኢየሩሳሌም አልሄድኩም፤ ነገር ግን አስቀድሜ ወደ ዐረብ አገር ሄድኩ፤ እንደገናም ወደ ደማስቆ ተመለስኩ። 18 ቀጥሎም ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋ የሚባለውን ጴጥሮስን ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም ሄድኩ፤ እዚያም ከእርሱ ጋር ዐሥራ አምስት ቀን ቈየሁ። 19 የጌታን ወንድም ያዕቆብን አየሁ እንጂ ከሌሎቹ ከሐዋርያት ማንንም አላየሁም። 20 ይህ የምጽፍላችሁ ሐሰት እንዳልሆነ በእግዚአብሔር ፊት አረጋግጥላችኋለሁ። 21 ከዚህ በኋላ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር ሄድኩ። 22 በይሁዳ ምድር ያሉት የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያን እኔን ፊት ለፊት አይተው ገና አላወቁኝም ነበር። 23 እነርሱ የሰሙት “ያ ቀድሞ ያሳድደን የነበረ ሰው ያን ሊያጠፋው ይፈልግ የነበረውን እምነት አሁን ይሰብካል” የሚል ቃል ነበር። 24 በእኔ ምክንያትም እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር። |