ዕዝራ 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምከአሕዛብ ጋር መጋባትን ለመከልከል የወጣ ሕግ 1 ዕዝራ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ለጸሎት ተንበርክኮ እያለቀሰ የተፈጸመውን ኃጢአት ሁሉ ለእግዚአብሔር በሚናዘዝበት ጊዜ ወንዶችም፥ ሴቶችም፥ ሕፃናትም ጭምር ያሉበት ቊጥሩ የበዛ የእስራኤል ማኅበር መጥቶ በዙሪያው በመሰብሰብ በመረረ ሁኔታ ያለቅሱ ነበር። 2 ከዚህም በኋላ ከዔላም ጐሣ የየሒኤል ልጅ ሸካንያ ዕዝራን እንዲህ አለው፦ “በእርግጥ እኛ በአካባቢአችን ካሉት አሕዛብ ባዕዳን ሴቶችን በማግባት በእግዚአብሔር ላይ የነበረንን እምነት አጓድለናል፤ ይህም ሁሉ ሆኖ አሁንም ለእስራኤል ተስፋ አለ። 3 አሁን እንግዲህ እነዚህን ባዕዳን ሴቶች ከነልጆቻቸው ማሰናበት እንደሚገባን ለአምላካችን ቃል እንግባ፤ አንተ ጌታዬና የአምላካችንን ትእዛዝ የሚያከብሩ ሌሎችም የምትሰጡንን ምክር ሁሉ እንፈጽማለን፤ የእግዚአብሔር ሕግ የሚያዘውን ሁሉ እናደርጋለን፤ 4 ይህንንም ሁሉ ለማስፈጸም ኀላፊነቱ የአንተ ስለ ሆነ ተነሥ፤ እኛም እንደግፍሃለን፤ አይዞህ በርታ።” 5 ስለዚህም ዕዝራ የካህናት፥ የሌዋውያንና የቀሩት ሕዝብ መሪዎች ሸካንያ ባቀረበው ሐሳብ መስማማታቸውን በመሐላ እንዲያረጋግጡለት በማድረግ ሥራውን ጀመረ። 6 ቀጥሎም ዕዝራ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ከነበረው ስፍራ በመነሣት የኤልያሺብ ልጅ ዮሐናን ወደሚኖርባቸው ክፍሎች ገባ፤ ምርኮኞቹ እምነት በማጓደል ስለ ፈጸሙትም በደል ሁሉ እያዘነ ሌሊቱን በዚያው አነጋ፤ እህልም ሆነ ውሃ አልቀመሰም። 7 ከምርኮ የተመለሱትም ሁሉ በኢየሩሳሌም ይሰበሰቡ ዘንድ በመላው ኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምድር ሁሉ ታወጀ። 8 ይህም ሁሉ በሕዝቡ መሪዎች ምክርና ትእዛዝ የተወሰነ ነበር፤ በሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ ወደዚህ ስብሰባ መምጣት ያልቻለ ማንም ሰው ቢኖር ንብረቱ ሁሉ እንደሚወረስና ከምርኮ ከተመቱት ሰዎች ጉባኤ እንደሚወገድ ተነገረው። 9 ይህም ጥሪ እንደ ተላለፈ በሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ በይሁዳና በብንያም ግዛት የሚኖሩት ሁሉ ዘጠነኛው ወር በገባ በሃያኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው በቤተ መቅደሱ አደባባይ ተሰበሰቡ፤ ሰዎቹ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት በተሰበሰቡበት ጉዳይና በዝናቡ ምክንያት እየተንቀጠቀጡ ቆመው ነበር። 10 ካህኑ ዕዝራም ቆሞ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “እነሆ እምነታችሁን አጓድላችሁ ተገኝታችኋል፤ ባዕዳን ሴቶችንም በማግባታችሁ ምክንያት በእስራኤል ላይ የበደልን ዕዳ አምጥታችኋል። 11 ከአሁን በኋላ እንግዲህ በቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአታችሁን ሁሉ ተናዘዙ፤ እርሱም ደስ የሚሰኝበትን ነገር ሁሉ አድርጉ፤ በምድራችን ከሚኖሩት ባዕዳን ሁሉ ራቁ፤ ያገባችኋቸውንም ባዕዳን ሴቶች ወዲያ አስወግዱ።” 12 የተሰበሰቡትም ሰዎች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “አንተ የምትለውን ሁሉ እናደርጋለን!” አሉ። 13 ንግግራቸውንም በመቀጠል እንዲህ አሉት፦ “እነሆ እዚህ የተሰበሰበው ሕዝብ ብዙ ነው፤ ከዚህም ጋር በከባድ ሁኔታ እየዘነበ ነው፤ መጠለያ በሌለበት በዚህ ስፍራ መቆም አልቻልንም፤ በዚህ ኃጢአት የተበከልነውም ብዙዎች በመሆናችን ይህን ሁሉ ነገር በአንድ ወይም በሁለት ቀኖች ውስጥ መፈጸም አይቻልም። 14 ስለዚህ አለቆቻችን በዚሁ በኢየሩሳሌም ጉዳዩን ያጥኑት፤ ከዚህም በኋላ ባዕድ ሴት ያገባ ሁሉ እያንዳንዱ በሚሰጠው የቀጠሮ ቀን ከሚኖርባት ከተማ መሪዎችና ዳኞች ጋር እየመጣ ውሳኔውን ይቀበል፤ እግዚአብሔር የተቈጣበትም ሁኔታ ሁሉ በዚሁ ዐይነት ይበርዳል።” 15 ይህም በተነገረ ጊዜ መሹላምና ሻበታይ ተብሎ የሚጠራው አንድ ሌዋዊ ድጋፍ ከሰጡአቸው ከዐሣሔል ልጅ ዮናታንና የቲቅዋ ልጅ ከሆነው ከያሕዘያ በቀር ሌላ ተቃዋሚ አልነበረም። 16 ከምርኮ የተመለሱት ሁሉ ይህንኑ ዕቅድ ለመቀበል ተስማሙ፤ ስለዚህም ካህኑ ዕዝራ ከጐሣ መሪዎች መካከል መርጦ አስፈጻሚዎችን በመሾም ስም ዝርዝራቸውን መዝግቦ አኖረ፤ እነርሱም ዐሥረኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን ጉዳዩን መመርመር ጀመሩ። 17 በሚቀጥለው ዓመት በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ከባዕዳን ሴቶች ጋር የተጋቡትን ሰዎች ጉዳይ በሙሉ መርምረው ጨረሱ። ከባዕዳን ሴቶች ጋር የተጋቡ ሰዎች ስም ዝርዝር 18 ከባዕዳን ሴቶች ጋር የተጋቡ ሰዎች ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው፦ የኢዮጼዴቅ ልጆች ከሆኑት ከኢያሱና ከወንድሞቹ ጐሣ የተገኙ፤ ማዕሤያ፥ ኤሊዔዘር፥ ያሪብና ገዳልያ፤ በየጐሣቸው የተመዘገቡ ካህናት፥ 19 እነርሱም ሚስቶቻቸውን ፈተው ለማሰናበት ቃል ከገቡ በኋላ ለኃጢአታቸው ማስተስረያ የሚሆን አንድ የበግ አውራ ለሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ። 20 ከኢሜር ጐሣ፦ ሐናኒና ዘባድያ። 21 ከሓሪም ጐሣ፦ ማዕሤያህ፥ ኤልያስ፥ ሸማዕያ፥ የሒኤልና ዑዚያ፤ 22 ከፓሽሑር ጐሣ፦ ኤልዮዔናይ፥ ማዕሤያ፥ እስማኤል፥ ናትናኤል፥ ዮዛባድና ኤልዓሳ፤ 23 ከሌዋውያን ወገን፦ ዮዛባድ፥ ሺምዒ፥ ቀሊጣ ተብሎ የሚጠራው ቄላያ፥ ፐታሕያ፥ ይሁዳና ኤሊዔዘር፤ 24 ከመዘምራን ወገን፦ ኤልያሺብ። ሻሉም፥ ጤሌምና ኡሪ፤ ከቤተ መቅደስ ዘብ ጠባቂዎች ወገን፦ 25 ከሌሎች እስራኤላውያን፦ ከፓርዖሽ ጐሣ፦ ራምያ፥ ይዚያ፥ ማልኪያ፥ ሚያሚን፥ አልዓዛር ማልኪያና በናያ፤ 26 ከዔላም ጐሣ፦ ማታንያ፥ ዘካርያስ የሒኤል፥ ዐብዲ፥ የሬሞትና ኤልያ፤ 27 ከዛቱ ጐሣ፦ ኤልዮዔናይ፥ ኤልያሺብ፥ ማታንያ፥ የሬሞት፥ ዘባድና ዓዚዛ፤ 28 ከቤባይ ጐሣ፦ የሆሐናን፥ ሐናንያ፥ ዛባይና ዐትላይ፤ 29 ከባኒ ጐሣ፦ መሹላም፥ ማሉክ፥ ዐዳያ፥ ያሹብ፥ ሸአልና የራሞት፤ 30 ከፓሐትሞአብ ጐሣ፦ ዓድና፥ ከላል፥ በናያ፥ ማዕሴያ፥ ማታንያ፥ በጻልኤል፥ ቢኑይና ምናሴ፤ 31-32 ከሓሪም ጐሣ፦ ኤሊዔዘር፥ ይሺያ፥ ማልኪያ፥ ሸማዕያ፥ ስምዖን፥ ብንያም፥ ማሉክና ሸማርያ፤ 33 ከሐሹም ጐሣ፦ ማታናይ፥ ማታታ፥ ዛባድ፥ ኤሊፌሌጥ፥ የሬማይ፥ ምናሴና ሺምዒ፤ 34-37 ከባኒ ጐሣ፦ መዕዳይ፥ ዓምራም፥ ኡኤል፥ በናያ፥ ቤድያ፥ ከሉሂ፥ ዋንያ፥ መሬሞት፥ ኤልያሺብ፥ ማታንያ፥ ማትናይና ያዕሱ፤ 38-42 ከቢኑይ ጐሣ፦ ሺምዒ፥ ሼሌምያ፥ ናታን፥ ዓዳያ፥ ማክናደባይ፥ ሻሻይ፥ ሻራይ፥ ዐዛርኤል፥ ሼሌምያ፥ ሸማርያ፥ ሻሉም፥ አማርያና ዮሴፍ፤ 43 ከነቦ ጐሣ፦ የዒኤል፥ ማቲትያ፥ ዛባድ፥ ዘቢና፥ ያዳይ፥ ኢዩኤልና በናያ፤ 44 እነዚህ ሁሉ ሰዎች ባዕዳን ሴቶችን አግብተው የነበሩ ናቸው፤ እነርሱም ያገቡአቸውን ባዕዳን ሴቶች ሁሉ ፈተው ከነልጆቻቸው አባረሩ። |