Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የኢየሩሳሌም መቀጣት

1 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ድምፁን ከፍ አድርጎ “ከተማይቱን የምትቀጡ እናንተ ወደዚህ ቅረቡ፤ ለማጥፋት የተዘጋጀ የጦር መሣሪያዎቻችሁንም ይዛችሁ ኑ!” ብሎ ሲናገር ሰማሁ።

2 ስድስት ሰዎችም የመግደያ መሣሪያዎቻቸውን ይዘው ወደ ሰሜን ከሚመለከተው ከላይኛው በር መጡ፤ ከእነርሱም መካከል በፍታ የለበሰና የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር በጐኑ የያዘ አንድ ሰው ነበር። ስድስቱም ሰዎች ገብተው በነሐሱ መሠዊያ አጠገብ ቆሙ።

3 ከዚህ በኋላ የእስራኤልን አምላክ ክብር የሚገልጥ ነጸብራቅ ቀድሞ ካረፈበት ከኪሩብ ላይ ተነሥቶ ወደ ቤተ መቅደሱ መግቢያ በር ሄደ፤ እግዚአብሔርም በፍታ የለበሰውንና የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር የያዘውን ሰው፥ ጠራው፤

4 “በመላዋ ኢየሩሳሌም ከተማ ተዘዋወር፤ በከተማይቱ ከተፈጸመውም አጸያፊና አሳፋሪ ነገር የተነሣ በመሠቀቅ ባዘኑት ሰዎች ግንባር ላይ ምልክት አድርግባቸው!” አለው።

5 እንደገናም እግዚአብሔር ሌሎቹን ሰዎች እንዲህ ሲላቸው ሰማሁ፦ “በሉ እናንተም እርሱን ተከትላችሁ በከተማይቱ ውስጥ በመዘዋወር ሁሉን ግደሉ፤ ለማንም በመራራት ምሕረት አታድርጉ።

6 ሽማግሌ ሆነ ወጣት ወንዶችና ሴቶች፥ ሕፃናትንና ሴቶችን ሁሉ ግደሉ፤ ነገር ግን በግንባሩ ላይ ምልክት ያለበትን ማንንም አትንኩ፤ ግድያውንም ከዚሁ ከቤተ መቅደሴ ጀምሩ፤” ስለዚህ እዚያ በቤተ መቅደስ ከቆሙት መሪዎች አንሥተው ግድያውን ማካሄድ ጀመሩ።

7 እግዚአብሔርም “ሂዱና ቤተ መቅደሱን አርክሱ! አደባባዩንም በሬሳ የተሞላ አድርጉ!” አላቸው፤ እነርሱም ወጥተው በከተማይቱ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ገደሉ።

8 ግድያውም በሚፈጸምበት ጊዜ እኔ ብቻዬን ቀርቼ ሳለሁ በግንባሬም ወደ መሬት ተደፍቼ በመጮኽ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! ወዮ! በእስራኤል የተረፉትን ሁሉ እስክትፈጅ ድረስ በኢየሩሳሌም ላይ ይህን ያህል ትቈጣለህን?” አልኩ።

9 እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፦ “የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ እጅግ የከፋ ኃጢአት በመሥራት በድለዋል፤ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ግድያ ፈጽመዋል፤ ከተማይቱንም በዐመፅ የተሞላች አድርገዋታል፤ ‘እግዚአብሔር አገራችንን ትቶአታል፤ እኛንም አይመለከተንም’ ይላሉ፤

10 ስለዚህ አልራራላቸውም፤ ምሕረትም አላደርግላቸውም፤ እነርሱ በሌሎች ላይ ያደረጉትን ሁሉ በእነርሱ ላይ መልሼ አደርግባቸዋለሁ።”

11 ከዚህ በኋላ ያ በፍታ የለበሰውና የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር የያዘው ሰው ተመልሶ መጥቶ “ያዘዝከኝን ሁሉ ፈጽሜአለሁ” ብሎ ለእግዚአብሔር ተናገረ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告