Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ለሕዝቅኤል የተገለጠለት ሁለተኛ ራእይ ባዕድ አምልኮ በኢየሩሳሌም
( 8፥1—10፥22 )

1 በተሰደድን በስድስተኛው ዓመት፥ በስድስተኛው ወር፥ በአምስተኛው ቀን፥ ከይሁዳ የተሰደዱት ሕዝብ መሪዎች በቤቴ ከእኔ ጋር አብረው ተቀምጠው ሳሉ፥ የልዑል እግዚአብሔር ኀይል ድንገት በእኔ ላይ ወረደ።

2 ቀና ብዬ ስመለከት መልኩ እንደ እሳት ነበልባል የሚያበራ የሰው አምሳያ አየሁ፤ ያም የሰው አምሳያ ከወገቡ በታች እሳት፥ ከወገቡ በላይ የሚያንጸባርቅ የጋለ ብረት ይመስል ነበር።

3 እርሱም የሰው እጅ የሚመስል ነገር ወደ እኔ ዘርግቶ የራስ ጠጒሬን ያዘ፤ በዚሁ ራእይ የእግዚአብሔር መንፈስ ከምድር ወደ ሰማይ አነሣኝና ወደ ኢየሩሳሌም አደረሰኝ። በሰሜን በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሚያስገባው ቅጽር በር አሳልፎ የእግዚአብሔርን ቅናት የሚቀሰቅስን የጣዖት ምስል ወዳለበት ስፍራ አደረሰኝ።

4 በዚያም የእስራኤል አምላክ ክብር ነበር፤ ይህም በኬባር ወንዝ ያየሁት ዐይነት ራእይ ነበር።

5 እግዚአብሔርም፦ “የሰው ልጅ ሆይ! በስተ ሰሜን በኩል ተመልከት!” አለኝ፤ በተመለከትኩም ጊዜ በቅጽር በሩ ፊት ለፊት ባለው መሠዊያ አጠገብ የእግዚአብሔርን ቅናት የሚቀሰቅስ ምስል ነበር።

6 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! የሆነውን ነገር ሁሉ ታያለህን? የእስራኤል ሕዝብ በዚህ ስፍራ የሚፈጽሙትን አጸያፊ ነገር ተመልከት፤ በዚህ አድራጎታቸው ከተቀደሰው ስፍራዬ እንድርቅ አድርገውኛል፤ ከዚህም የበለጠ እጅግ አስነዋሪ የሆነ ነገር ገና ታያለህ።”

7 በውጪ በኩል ወዳለው አደባባይ መግቢያ በር ወሰደኝ፤ በቅጽሩ ግንብ ላይ አንድ ቀዳዳ ነበር፤

8 “የሰው ልጅ ሆይ! በዚህ በኩል ግንቡን ሸንቊረው” አለኝ፤ በሸነቈርኩትም ጊዜ አንድ በር አገኘሁ፤

9 እርሱም “ወደ ውስጥ ግባና በዚያ የሚያደርጉትን ክፉና አጸያፊ ነገር ተመልከት!” አለኝ።

10 እኔም ወደ ውስጥ ገብቼ ተመለከትኩ፤ በግንቡ ዙሪያ በደረታቸው የሚሳቡ ንጹሕ ያልሆኑ እንስሶችና የእስራኤል ሕዝብ ጣዖቶች ተስሎበት ነበር።

11 የሻፋንን ልጅ አዛንያን ጨምሮ ሰባ የእስራኤላውያን መሪዎች በዚያ ነበሩ፤ እያንዳንዱም ጥና ይዞ ነበር፤ ከጥናውም መልካም መዓዛ ያለው የዕጣን ጢስ ይወጣ ነበር፤

12 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “የእስራኤል መሪዎች በየራሳቸው ጣዖት ቤት በጨለማ ሆነው እግዚአብሔር አያየንም! ምድሪቱንም ትቶአታል በማለት የሚያደርጉትን ታያለህን?” አለኝ።

13 እርሱም እንደገና “ከዚህም እንኳ የሚበልጥ አጸያፊ ነገር ሲያደርጉ ታያቸዋለህ” አለኝ፤

14 ስለዚህ በስተሰሜን በኩል ወዳለው ወደ ቤተ መቅደሱ ቅጽር በር ወሰደኝ፤ ተሙዝ ለተባለው ጣዖታቸው ሴቶች ሲያለቅሱለት አሳየኝ።

15 እርሱም “የሰው ልጅ ሆይ! ይህን ታያለህን? ገና ከዚህ የባሰ አጸያፊ ነገር ታያለህ” አለኝ።

16 ስለዚህ በውስጥ በኩል ወዳለው ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ወሰደኝ፤ እዚያም ወደ መቅደሱ መግቢያ አጠገብ በመሠዊያውና በመተላለፊያው መካከል ኻያ አምስት ያኽል ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ጀርባቸውን ወደ መቅደሱ አድርገው የምትወጣዋን ፀሐይ በማምለክ ወደ ምሥራቅ ተንበርክከው ይሰግዱ ነበር።

17 ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ይህን ታያለህን? እነዚህ የይሁዳ ሕዝቦች በዚህ ስፍራ ያየኸውን አጸያፊ ነገር ሁሉ በመሥራትና በአገሪቱም ላይ ዐመፅ ማስፋፋቱ አልበቃ ብሎአቸው ወደዚህ ወደ ቤተ መቅደስ እንኳ ሳይቀር በቀጥታ መጥተው ይህን ሁሉ በማድረግ እኔን እንደገና ማስቈጣት ይፈልጋሉ፤ እንዴት እንደሚሰድቡኝና እኔን ለማስቈጣት የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተመልከት!

18 ስለዚህ ቊጣዬን አወርድባቸዋለሁ፤ ራርቼም አልተዋቸውም፤ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ወደ እኔ ቢጮኹም አላደምጣቸውም።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告