Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእስራኤል መጨረሻ መቃረብ

1 እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦

2 “የሰው ልጅ ሆይ! እኔ ልዑል እግዚአብሔር ስለ እስራኤል ምድር የምለው ይህ ነው፤ በሁሉም አቅጣጫ የዚህች ምድር የመጨረሻ መጥፊያ ደርሶአል።

3 “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! አሁን መጥፊያችሁ ደርሶአል። ቊጣዬን አወርድባችኋለሁ፤ እንደ አካሄዳችሁም እፈርድባችኋለሁ ስለ ርኲሰታችሁም ሁሉ እቀጣችኋለሁ።

4 ከቶ አልራራላችሁም፤ ምሕረትም አላደርግላችሁም። በርኲሰት ላይ እስካላችሁ ድረስ እንደ አካሄዳችሁ እቀጣችኋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።”

5 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “መከራ በመከራ ላይ ይመጣባችኋል፤

6 መጨረሻው መጥቶአል፤ መጨረሻው ደርሶአል፤ በእናንተ ላይ ተነሥቶአል፤ እነሆ፥ መጥቶአል።

7 በምድሪቱ የምትኖሩ ሕዝብ ሁሉ የመጥፊያችሁ ጊዜ ደርሶአል፤ ጊዜው ደርሶአል፤ ቀኑም ቀርቦአል፤ እርሱም የሁከት ቀን ነው እንጂ በከፍተኛ ቦታዎች የመፈንጠዣ ቀን አይደለም።

8 “አሁን እኔ በቅርቡ ቊጣዬንና መዓቴን አወርድባችኋለሁ፤ እንዳካሄዳችሁም እፈርድባችኋለሁ፤ በአጸያፊ ድርጊታችሁም ምክንያት እቀጣችኋለሁ።

9 ከቶ አልራራላችሁም፤ ምሕረትም አላደርግላችሁም፤ በርኲሰት ላይ እስካላችሁ ድረስ እንደ አካሄዳችሁ እቀጣችኋለሁ፤ በዚያን ጊዜ የምቀጣችሁ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።”

10 እነሆ፥ የጥፋት ቀን በእስራኤል ላይ ሊመጣ ተቃርቦአል፤ ግፍና ዐመፅ በዝቶአል፤ ትዕቢትም ከፍ ከፍ ብሎአል።

11 ከዐመፅ የተነሣ ክፉ ሥራ በዝቶአል፤ ከእነርሱ መካከል አንዳቸውም አይተርፉም። ከብልጽግናቸውና ከተትረፈረፈ ሀብታቸው አንድ ነገር እንኳ አይኖርም።

12 እነሆ ጊዜው ደርሶአል፤ ቀኑም ቀርቦአል፤ የእኔ የእግዚአብሔር ቊጣ በሁሉም ላይ ስለሚመጣ ገዢ አይደሰት፤ ሻጭም አይዘን።

13 ሻጭና ገዢ በሕይወት እስካሉ ድረስ ሻጭ የሸጠውን ዕቃ መልሶ ሊያገኘው እንደማይችል ሁሉ እንዲሁም ራእዩ የተነገረው ስለ ሁሉም ስለ ሆነ ሊታጠፍ አይችልም። እነርሱም ስለ በበደሉ ሕይወታቸውን ማዳን አይችሉም።

14 መለከት ይነፋል ሁሉ ነገር ይዘጋጃል፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቊጣ በሰው ሁሉ ላይ ስለሚገለጥ ማንም ወደ ጦርነት አይሄድም።


በእስራኤል ኃጢአት ምክንያት የሚመጣው ቅጣት

15 ውጪ ጦርነት፥ በየቤቱም በሽታና ራብ አለ፤ ከከተማ ውጪ የሚኖር ሁሉ በጦርነት ይሞታል፤ በከተማም ያለ በበሽታና በረሀብ ይመታል።

16 የሸለቆ ርግቦች ራሳቸውን ለማዳን ወደ ተራራ እንደሚወጡ እንዲሁም ከሰዎቹ መካከል ከሞት የተረፉ ካሉ በተራራ ላይ ተገኝተው በኃጢአታቸው ምክንያት እንደ ሸለቆ ርግቦች የሐዘን እንጒርጒሮ ያሰማሉ።

17 እጆች ሁሉ ይዝላሉ፤ ጒልበቶች ሁሉ ይብረከረካሉ፤

18 ማቅ ይለብሳሉ፤ ድንጋጤ ይይዛቸዋል፤ በፊቶቻቸው ላይ ኀፍረት ይታያል፤ ራሳቸውንም ይላጫሉ።

19 ብራቸውን በየመንገዱ ላይ ይወረውራሉ፤ ወርቃቸውም እንደ ርኩስ ነገር ይቈጠራል፤ ብርና ወርቃቸው በእግዚአብሔር ቊጣ ቀን አያድኑአቸውም፤ ራባቸውን አያስወግዱላቸውም፤ ወይም ሆዳቸውን አይሞሉላቸውም፤ በኃጢአት ለመውደቃቸው ምክንያት የሆኑባቸው እነርሱ ናቸው።

20 መመኪያቸው ከሆኑት ውብ ጌጦቻቸው አስጠሊና አጸያፊ ጣዖቶቻቸውን ሠሩባቸው፤ ስለዚህ እነዚህን ጌጦቻቸውን በእነርሱ ዘንድ አረክሳቸዋለሁ።

21 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ጌጦቻችሁን ለባዕዳን በምርኮ፥ ለምድር ኃጢአተኞችም በብዝበዛ መልክ አሳልፌ እሰጣለሁ። እነርሱም ያረክሱታል።

22 ወንበዴዎች ወደ ቤተ መቅደሴ ገብተው ያረክሱታል። ሲያረክሱትም አልከለክላቸውም።

23 “ሀገሪቱ በነፍስ ግድያ ወንጀል፥ ከተማይቱ በዓመፅ ስለ ተሞሉ የማሰሪያ ሰንሰለት አዘጋጅ።

24 በሕዝቦች መካከል እጅግ የከፉትን ወደዚህ አምጥቼ ቤቶቻችሁን እንዲወርሱ አደርጋለሁ፤ የኀያላንን ትዕቢት አጠፋለሁ፤ የተቀደሱ ቦታዎቻችሁንም ያረክሳሉ።

25 ጭንቀት በሚመጣበት ጊዜ ሰላምን ትሻላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙም፤

26 አንዱ መቅሠፍት ሌላውን ያስከትላል፤ አንዱ ወሬም ሌላውን ወሬ ተከታትሎ ይመጣል፤ ነቢያት ያዩትን ራእይ እንዲነግሩአችሁ ትለምኑአቸዋላችሁ፤ ካህናት ሕዝቡን የሚያስተምሩት ሕግ፥ ሽማግሌዎችም ለሕዝቡ የሚሰጡት ምክር ጠፋባቸው።

27 ንጉሡ ያለቅሳል፤ መስፍኑም ሙሉ በሙሉ ተስፋ ይቈርጣል፤ ሕዝቡም ከፍርሃት የተነሣ ይርበደበዳሉ፤ እንደ አካሄዳችሁ እቀጣችኋለሁ፤ በሌሎች ላይ በፈረዳችሁት ዐይነት እፈርድባችኋለሁ፤ በዚህም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告