Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔር የጣዖት አምልኮን መቃወሙ

1 እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፥

2 “የሰው ልጅ ሆይ! ወደ እስራኤል ተራራዎች ተመልከት፤ በእነርሱም ላይ ትንቢት ተናገር።

3 የእስራኤል ተራራዎች የልዑል እግዚአብሔርን ቃል እንዲሰሙ ንገራቸው፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምናገረውን ተራራዎች፥ ኮረብቶችንና ገደላማ ሸለቆዎች ሁሉ ይስሙ፤ ሕዝቦች ለጣዖቶች የሚሰግዱባቸውን ከፍተኛ ቦታዎች ሁሉ የሚያጠፋ ሰይፍ እልካለሁ።

4 መሠዊያዎች ሁሉ ይፈርሳሉ፤ የዕጣን ማቅረቢያዎች ሁሉ ይሰባበራሉ፤ የተገደሉትም ሰዎች በጣዖቶቻቸው ፊት ይጣላሉ።

5 የእስራኤል ሕዝብ ሬሳቸው በጣዖቶቻቸው ፊት እንዲወድቅ አደርጋለሁ፤ አጥንቶቻቸውንም በየመሠዊያቸው ዙሪያ እበትነዋለሁ።

6 የምትኖሩባቸው ከተሞቻችሁ ሁሉ ባድማ ይሆናሉ፤ የመስገጃ ከፍተኛ ቦታዎቻችሁም ይፈርሳሉ፤ መሠዊያዎቻችሁ ፈርሰው ውድማ ይሆናሉ፤ ጣዖቶቻችሁ ተንኰታኲተው ይወድቃሉ፤ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁም ይሰባበራሉ፤ የሠራችሁት ነገር ሁሉ እንዳልነበረ ይሆናል።

7 የተገደሉት በአካባቢያችሁ ይጣላሉ፤ ከዚያ በኋላ እናንተ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።

8 “ነገር ግን ጥቂቶቻችሁ እንድትተርፉ አደርጋለሁ፤ ጥቃቶቻችሁ ወደ ሌሎች ሕዝቦች በመሄድ ከጦርነት አምልጣችሁ በተለያዩ አገሮች ትበተናላችሁ።

9 ከሞት ያመለጣችሁት እናንተ ተማርካችሁ በሄዳችሁበት ሕዝቦች መካከል ታስታውሱኛላችሁ፤ የምታስታውሱኝም ከእኔ በራቀው ሥርዓተ አልባ በሆነው ክፉ ልባችሁና ሥርዓተ አልባ በሆነው ዐይናችሁ ጣዖቶችን በመመልከት ስላሳዘናችሁኝ ነው። በርኩስ ድርጊቶቻችሁም ላደረጋችሁት ክፉ ነገር ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ።

10 እኔ እግዚአብሔር መሆኔንና ጥፋት እንደማመጣባቸው የሰጠሁት ማስጠንቀቂያ ሁሉ ከንቱ ዛቻ እንዳልሆነ ይገነዘባሉ።”

11 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በጦርነት፥ በራብና በቸነፈር ስለሚመቱ ስለ እስራኤላውያን ክፉ ርኲሰት ሁሉ ወዮ! እያላችሁ እጆቻችሁን እያማታችሁና በእግሮቻችሁ እየረገጣችሁ ሐዘናችሁን ግለጡ!

12 በሩቅ ያሉት ታመው ይሞታሉ፤ በቅርብ ያሉትም በጦርነት ይገደላሉ፤ ከዚያ የሚተርፉትም በራብ ያልቃሉ፤ በዚህም ዐይነት ኀይል የተሞላበትን ቊጣዬን በእነርሱ ላይ እፈጽማለሁ።

13 ሬሳዎች በጣዖቶችና በመሠዊያዎች ዙሪያ ይከመራሉ፤ በከፍተኛ ኰረብቶችና በተራሮች ጫፍ ላይ፥ እንዲሁም በየለምለሙ ዛፍና በየትልልቁ ወርካ ሥር ለጣዖቶቻቸው መልካም ሽታ ባቀረቡባቸው ስፍራዎች ሁሉ ሬሳዎች ይወድቃሉ፤ በዚያን ጊዜ ሰዎች ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።

14 በእርግጥም እጄን ዘርግቼ አገራቸውን አጠፋታለሁ፤ ከደቡባዊው በረሓ አንሥቶ በሰሜን በኩል እስከምትገኘው እስከ ሪብላ ከተማ ድረስ ባድማ አደርጋታለሁ፤ እስራኤላውያን የሚኖሩበትን ስፍራ ሁሉ አንድም ሳይቀር አጠፋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንድ አሆንኩ ሰዎች ሁሉ ያውቃሉ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告