ሕዝቅኤል 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሕዝቅኤል ጠጒሩን መላጨቱ 1 እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! የተሳለ ሰይፍ ወስደህ ጢምህንና የራስ ጠጒርህን በሙሉ ተላጭ፤ ጠጒርህንም በሚዛን መዝነህ በሦስት ቦታ ክፈለው። 2 ከበባው ከተፈጸመ በኋላ ከሦስቱ አንዱን እጅ የከተማውን ንድፍ በሠራህበት ጡብ መካከል አቃጥለው፤ ሁለተኛውን አንድ ሦስተኛ እጅ ቈራርጠህ የከተማው ንድፍ በተሠራበት ጡብ ዙሪያ አኑረው። ሦስተኛውን አንድ ሦስተኛ እጅ ደግሞ ለነፋስ በትነው፤ እኔም በሰይፍ አሳድደዋለሁ። 3 በከተማው ዙሪያ በሰይፍ ቈራርጠው፤ ደግሞም ከዚሁ ጥቂት ጠጒር ወስደህ በመጐናጸፊያህ ጫፍ ላይ ቋጥረው። 4 ከእርሱም ላይ እንደገና ጥቂት ቈንጥረህ በእሳት ውስጥ ጣለውና እንዲቃጠል አድርገው፤ ከእርሱም የሚነሣው እሳት ወደ እስራኤል ሕዝብ ሁሉ ይደርሳል።” 5 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነሆ ኢየሩሳሌምን ተመልከት! ሌሎች አገሮች በዙሪያዋ ሆነው በሕዝቦች መካከል እንድትሆን አድርጌአታለሁ፤ 6 ኢየሩሳሌም ግን ሕጎቼንና ደንቤን በመጣስ ከሌሎች ሕዝቦች ይልቅ የከፋችና በዙሪያዋም ካሉት አገሮች ይበልጥ እምቢተኛ መሆንዋን አሳይታለች፤ ኢየሩሳሌም ሕጎቼንና ደንቦቼን ንቃለች፤ ትእዛዞቼንም አልተከተለችም።” 7 ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር የሚለው እንዲህ ነው፦ “እናንተ የኢየሩሳሌም ኗሪዎች! በዙሪያችሁ ካሉት ሕዝቦች ይበልጥ ሥርዓተ አልበኞች ሆናችኋል፤ ሕጎቼንና ሥርዓቴን አላከበራችሁም፤ በአካባቢአችሁ ባሉት ሕዝቦች ሥርዓት እንኳ አልተመራችሁም። 8 በዚህም ምክንያት እኔ ልዑል እግዚአብሔር በአንቺ በኢየሩሳሌም ላይ በቊጣ የተነሣሁብሽ መሆኔን እገልጥልሻለሁ፤ ሕዝቦች ሁሉ እያዩ በፍርድ እቀጣሻለሁ። 9 በርኲሰቶችሽ ሁሉ ምክንያት ከዚህ በፊት ያላደረግኹትንና ወደፊትም የማላደርገውን ቅጣት በአንቺ ላይ አመጣለሁ። 10 በዚህም ምክንያት በኢየሩሳሌም ያሉ ወላጆች በእርግጥ ልጆቻቸውን ይበላሉ፤ ልጆችም ወላጆቻቸውን ይበላሉ፤ በዚህ ዐይነት ሁላችሁንም እቀጣለሁ፤ የተረፉትንም በአራቱ ማእዘን እበትናቸዋለሁ። 11 “ስለዚህ ሕያው አምላክ እንደ መሆኔ እኔ እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ ክፋትና ርኲሰት የተሞላበት ነገር ሁሉ በመፈጸም ቤተ መቅደሴን በማርከሳችሁ ምክንያት እኔም ያለ ምሕረት እንድትዋረዱ አደርጋለሁ። 12 ከሕዝባችሁ አንድ ሦስተኛው እጅ በራብና በበሽታ ያልቃል፤ አንድ ሦስተኛው ከከተማው ውጪ በሰይፍ ይገደላል፤ ሌላው ሦስተኛ እጅ በአራቱ ማእዘን በነፋስ እንዲበተን አድርጌ በኋላ በሰይፍ አሳድደዋለሁ። 13 “ቊጣዬ በእርሱ ላይ ይፈጸማል ኀይለኛ ቊጣዬንም በእነርሱ ላይ አውርጄ እረካለሁ ይህንንም ቊጣዬን በእነርሱ ላይ ባወረድኩ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር በቅናቴ የተናገርኩ መሆኔን ያውቃሉ። 14 እንዲሁም አገራችሁን ባድማና በአካባቢአችሁ ለሚኖሩ ሕዝቦች መሳለቂያ አደርጋለሁ፤ ይህንንም የማደርገው አላፊ አግዳሚ ሁሉ እያየ ነው። 15 “በኀይለኛ ቊጣዬ በእናንተ ላይ ፍርዴን ተግባራዊ አድርጌ በምቀጣችሁ ጊዜ በአካባቢአችሁ ለሚኖሩ ሕዝቦች የመሳለቂያ፥ የሽሙጥ፥ የማስጠንቀቂያ የድንጋጤ ምክንያት ትሆናላችሁ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 16 እንደ ገዳይ ቀስት የሆነውን ራብ የማመጣባችሁ እንዲያጠፋችሁ ነው፤ ደጋግሜ ራብን አመጣባችኋለሁ፤ የምግብ አቅርቦታችሁም እንዲቋረጥ አደርጋለሁ። 17 ራብንና የዱር አራዊትን እለቅባችኋለሁ፤ ልጆቻችሁንም ይገድላሉ፤ ጦርነትንም አመጣባችኋለሁ፤ መቅሠፍትና ግድያም በመካከላችሁ ይስፋፋል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” |