ሕዝቅኤል 48 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየምድሪቱ አከፋፈል 1 ምድሪቱን ለመካፈል የተመዘገቡት ነገዶች እነዚህ ናቸው፤ የዳን ነገድ በምድሪቱ ሰሜናዊ ወሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ እርሱም ከሔትሎን ወደ ሐማት መግቢያ የሚወስደውን ጐዳና ተከትሎ ከዚያም ሐጻርዔኖንና የደማስቆ ሰሜናዊ ክፍል ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የዳን ድንበር ይሆናል። 2 አሴርም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከዳን ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ 3 ንፍታሌም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከአሴር ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ 4 ምናሴ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከንፍታሌም ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ 5 ኤፍሬም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከምናሴ ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ 6 ሮቤል ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከኤፍሬም ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ 7 ይሁዳ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከሮቤል ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል። በምድሪቱ ማእከል የሚከለል ልዩ ቦታ 8 ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከይሁዳ ነገድ ድንበር ጋር የተያያዘ ቦታ ለይታችሁ ትመደባላችሁ፤ ይህም ቦታ ወርዱ ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመት ከሌሎች ነገዶች ድርሻ ጋር ከምሥራቅ ጐን እስከ ምዕራብ ጐን ድረስ እኩል ይሆናል፤ ቤተ መቅደሱም የሚገኘው በዚህ ቦታ መካከል ነው። 9 በዚህም ክልል መካከል ርዝመቱ ኻያ አምስት ሺህ ክንድ፥ ወርዱም ኻያ ሺህ ክንድ የሆነ ቦታ ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናል። 10 ካህናቱም ከዚህ ከተቀደሰው ቦታ የተወሰነ ድርሻ ይኖራቸዋል፤ እርሱም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመትና ከሰሜን እስከ ደቡብ ዐሥር ሺህ ክንድ ወርድ ይኖረዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም በመካከሉ ይኖራል። 11 ይህም ቦታ የሳዶቅ ተወላጆች ለሆኑት የተቀደሱ ካህናት የተለየ ይሆናል። እስራኤላውያን ሁሉና ሌሎቹ ሌዋውያን እኔን ትተው በባዘኑ ጊዜ የሳዶቅ ልጆች ከትእዛዞቼ ፈቀቅ ሳይሉ ጠብቀው የኖሩ ናቸው። 12 ከተቀደሰው ቦታ ይህ የእነርሱ ድርሻ ነው፤ እርሱም በጣም የተቀደሰ ሲሆን ከሌዋውያን ድንበር ጋር የተያያዘ ነው። 13 ከካህናቱ ቦታ ጐን ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመትና ዐሥር ሺህ ክንድ ወርድ የሆነ የሌዋውያን ድርሻ አለ፤ ጠቅላላውም ከካህናቱ ድርሻ ጋር ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመትና ኻያ ሺህ ክንድ ወርድ ነው። 14 ለእግዚአብሔር የሚከለለው ስፍራ በምድሪቱ ከሚገኘው ሁሉ የተሻለ ምርጥ ቦታ ነው፤ ከእርሱም ተከፍሎ የሚሸጥና የሚለወጥ ወይም ለማንም በውርስ የሚተላለፍ አይሆንም፤ እርሱ ለእግዚአብሔር ተለይቶ የተቀደሰ ስፍራ ነው። 15 ልዩ ከሆነው ክልል ተከፍሎ የሚቀረው ስፍራ ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመት አምስት ሺህ ክንድ ወርድ ነው፤ እርሱም በአጠቃላይ ለሕዝቡ የጋራ መጠቀሚያ ይሆናል፤ ለቤት ሥራና ለከብት ማሰማሪያም ይሆናል፤ ከተማይቱም በመካከሉ ትሆናለች። 16 እርስዋም አራት ማእዘን እኩል ርዝመት ያላት ሆና የእያንዳንዱ ማእዘን ርዝመት አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል። 17 ከተማዋ በአራቱም ማእዘን የመሰማሪያ ቦታ ይኖራታል፤ በየማእዘኑ ያለው የመሰማሪያ ቦታ ስፋት ሁለት መቶ ኀምሳ ክንድ ነው። 18 ከተቀደሰው ክልል በምሥራቅ ዐሥር ሺህ ክንድ በምዕራብ ዐሥር ሺህ ክንድ ተነሥቶለት ከተማይቱ ከተሠራች በኋላ የሚቀረው ትርፍ ቦታ በከተማይቱ ለሚኖሩት ሕዝብ የእርሻ መሬት ይሆናል። 19 በከተማይቱ የሚኖር ከየትኛውም ነገድ የተወለደ ሰው ሁሉ ያን መሬት ማረስ ይችላል። 20 ስለዚህም በምድሪቱ መኻል የተለየው ቅዱስ ድርሻ በጠቅላላው የእያንዳንዱ ማእዘን ርዝመት ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ሲሆን እርሱም ከተማይቱ የተሠራችበትን ቦታ ያጠቃልላል። 21 በተቀደሰው ቦታና በከተማውም ይዞታ በሁለቱም በኩል የተረፈው ክፍል የመስፍኑ ድርሻ ነው። ይኸውም በምሥራቅ በኩል የተቀደሰውን ቦታ ከሚያዋስነው ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ተነሥቶ እስከ ምድሪቱ ወሰን ድረስ ነው። በምዕራብም በኩል የተቀደሰውን ቦታ ከሚያዋስነው ከኻያ አምስት ሺህ ክንድ ተነሥቶ እስከ ምድሪቱ ወሰን ድረስ ነው። የመሪውም ድርሻ ርዝመቱ ከሌሎቹ ነገዶች ድርሻ እኩል ነው። በዚህ ዐይነት የተቀደሰው ቦታና ቤተ መቅደሱ በመካከል ይሆናሉ ማለት ነው። 22 እንደዚሁም የሌዋውያኑና የከተማው ይዞታ በምሥራቅና በምዕራብ የመሪው ይዞታ ከሆኑት ቦታዎች መካከል ናቸው ማለት ነው፤ እንዲሁም በሰሜን ከይሁዳ ዕጣ፥ በደቡብም ከብንያም ዕጣ ጋር ይዋሰናል። ለሌሎች ነገዶች የተከፈለ ምድር 23 ስለቀሩትም ነገዶች የምድሪቱ አከፋፈል እንደሚከተለው ነው፤ ብንያም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የሚደርስ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ 24 ስምዖን ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከብንያም ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ 25 ይሳኮር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከስምዖን ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ 26 ዛብሎን ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከይሳኮር ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ 27 ጋድ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከዛብሎን ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል። 28 የጋድ ደቡባዊ ድንበር ከታማር ከተማ ደቡብ ተነሥቶ በመሪባ ቃዴስ እስከምትገኘው የውሃ ምንጭ ይዘልቃል፤ ከዚያም የግብጽ ወሰን የሆነውን ወንዝ ተከትሎ እስከ ሜዲቴራኒያን ባሕር ይደርሳል። 29 ልዑል እግዚአብሔር “በዚህ ዐይነት ለእስራኤል ነገዶች ሁሉ በርስትነት የምታከፋፍሉአቸው ምድር ይህች ናት” ሲል ተናገረ። የኢየሩሳሌም ቅጽር በሮች 30-31 የከተማይቱ መውጫ በሮች አራት ማእዘኖች የሚከተሉት ናቸው፦ በየማእዘኑ ሦስት በሮች ሲኖሩ ለያንዳንዱ በር የአንድ ነገድ ስም ተሰጥቶታል። በሰሜን በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ርዝመት አለው። በዚህ ማእዘን ያሉት ሦስት በሮች በሮቤል፥ በይሁዳና በሌዊ ስም ተሰይመዋል። 32 በምሥራቅ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ርዝመት አለው። በዚህ ማእዘን ያሉት ሦስት በሮች በዮሴፍ፥ በብንያምና በዳን ስም ተሰይመዋል። 33 በደቡብ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ርዝመት አለው። በዚህም ማእዘን ያሉት ሦስት በሮች በስምዖን፥ በይሳኮርና በዛብሎን ስም ተሰይመዋል። 34 በምዕራብ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ርዝመት አለው። በዚህም ማእዘን ያሉት ሦስት በሮች በጋድ፥ በአሴርና በንፍታሌም ስም ተሰይመዋል። 35 በአራቱም አቅጣጫ ያሉት የከተማይቱ የቅጽር ግንቦች ጠቅላላ ርዝመት ዐሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፤ ከአሁን በኋላ የከተማይቱ መጠሪያ ስም “እግዚአብሔር በዚያ አለ!” የሚል ይሆናል። |