Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 47 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ከቤተ መቅደሱ ሥር የሚፈልቀው ውሃ

1 ከዚያም በኋላ ወደ ቤተ መቅደሱ መግቢያ መለሰኝ፤ እዚያም ከቤተ መቅደሱ መድረክ ሥር ውሃ ወደ ምሥራቅ ይፈስ ነበር፤ (ይህም የቤተ መቅደሱ በር ወደ ምሥራቅ ዞሮ ስለ ነበረ ነው) ውሃውም የሚፈሰው ከቤተ መቅደሱ በስተደቡብ በኩል ባለው መድረክ ሥር ከመሠዊያው በስተደቡብ ነበር።

2 ያም ሰው በሰሜኑ ቅጽር በር በኩል ከቤተ መቅደሱ አውጥቶ ወሰደኝ፤ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ በሚመለከተውም ቅጽር በር አዞረኝ፤ ከቅጽር በሩም በስተ ደቡብ ውሃው ወደ ምሥራቅ ይፈስ ነበር።

3 ያም ሰው በያዘው የመለኪያ ገመድ ወደ ምሥራቅ የሚፈሰውን ውሃ በመከተል አንድ ሺህ ክንድ ለካ፤ በዚያም ውሃ እየተራመድኩ እንድሻገር አደረገኝ፤ ውሃውም እስከ ቊርጭምጭሚቴ ደረሰ።

4 እንደገናም አንድ ሺህ ክንድ ለካና እንድራመድ አደረገኝ፤ ውሃውም እስከ ጒልበቴ ደረሰ፤ ቀጥሎም አንድ ሺህ ክንድ ለክቶ በውሃው ውስጥ እንድራመድ አደረገኝ፤ ውሃውም እስከ ወገቤ ደረሰ።

5 እንደገናም አልፎ አንድ ሺህ ክንድ ለካ፤ ውሃው ጥልቅ ስለ ነበረ ልሻገረው የማልችል ወንዝ ሆነ፤ እርሱም ሊራመዱበት የማይቻል ለዋና ግን በቂ ጥልቀት ነበረው።

6 ሰውየውም “የሰው ልጅ ሆይ! ይህን ሁሉ በጥንቃቄ አስታውስ” አለኝ። ከዚያን በኋላ ያ ሰው ወደ ውሃው ዳርቻ መለሰኝ፤

7 እዚያም እንደ ደረስኩ በወንዙ ግራና ቀኝ ስመለከት ብዙ ዛፎችን አየሁ፤

8 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “ይህ ውሃ በምድሪቱ ውስጥ ወደ ምሥራቅ፥ ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆና ወደ ሙት ባሕር ይፈስሳል፤ ወደ ሙት ባሕር በሚፈስበት ጊዜ የጨዉ ባሕር ታድሶ ጥሩ ውሃ ይሆናል።

9 ውሃው በሚፈስበት ስፍራ ሁሉ ልዩ ልዩ ዐይነት እንስሶችና ዓሣም በብዛት ይገኛል፤ የወንዙ ፈሳሽ በሙት ባሕር የሚገኘውን በማደስ ያጠራዋል፤ በሚፈስበትም ቦታ ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል።

10 ከዔንገዲ ጀምሮ እስከ ዔንዔግላይም ድረስ ዓሣ አጥማጆች ይቆማሉ፤ ያም ቦታ መረቦች የሚዘረጉበት ቦታ ይሆናል፤ በሜዲትራኒያን ባሕር እንደሚገኘው ዐይነት በዚህም ልዩ ልዩ ዓሣ ይገኛል።

11 ነገር ግን ረግረጉና እቋሪው ውሃ የጨው መከማቻ እንደ ሆነ ይቀራል እንጂ የጠራ ውሃ አይሆንም።

12 በፈሳሹ ውሃ ዳርና ዳር ለምግብ የሚሆኑ ተክሎች በየዐይነቱ ይገኛሉ፤ እነርሱም ቅጠሎቻቸው አይደርቁም፤ ፍሬ ማፍራትንም አያቋርጡም፤ ከቤተ መቅደሱ ሥር የሚፈሰውን ወንዝ ውሃ ስለሚያገኙ በየወሩ አዲስ ፍሬ ያፈራሉ፤ ዛፎቹ ፍሬአቸው ለምግብ፥ ቅጠላቸው ለፈውስ የሚጠቅም ነው።”


የምድሪቱ ወሰኖች

13 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ለዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ በርስትነት የምታካፍላቸው የመሬት ድንበር የሚከተለው ነው፤ የዮሴፍ ነገድ ሁለት ድርሻ ይኖረዋል።

14 እኔ ለቀድሞ አባቶቻችሁ ይህችን ምድር ርስት አድርጌ ልሰጣቸው በመሐላ ቃል ገብቼላቸዋለሁ፤ አሁንም እናንተ ሁላችሁ እኩል ተከፋፈሉት፤ ይህም ምድር በርስትነት የእናንተ ይሆናል።

15 “የመሬቱ ድንበር እንደሚከተለው ነው፦ የሰሜኑ ድንበር ከሜዲቴራኒያን ባሕር ተነሥቶ ወደ በሔትሎን በኩል ወደ ሐማት መተላለፊያ፥ ወደ ጼዳድም፥

16 በደማስቆና በሐማት መካከል ወደሚገኙት ወደ ቤሮታና ሲብራይም ከተሞች፥ በሐውራን ጠረፍ ወደምትገኘው ወደ ቲኮን ከተማ እስከ ምሥራቅ ይዘልቃል።

17 በዚህም መሠረት ድንበሩ ከሜዲቴራኒያን ባሕር ተነሥቶ እስከ ሐጻር ዔኖን፥ እርሱም በደማስቆና በሐማት ድንበር በስተሰሜን እስካለው ቦታ ድረስ ይደርሳል፤ ይህም የሰሜኑ ድንበር ነው።

18 “የምሥራቁ ድንበር በደማስቆና በሐውራን መካከል አልፎ በዮርዳኖስ በኩል፥ በጊልዓድና በእስራኤል ምድር መካከል አልፎ ወደ ሙት ባሕርና እስከ ታማር ድረስ ነው። ይህም የምሥራቁ ድንበር ይሆናል።

19 “የደቡቡም ድንበር ከታማር ተነሥቶ እስከ መሪባ ቃዴስ ድረስ፥ ከዚያም ከግብጽ ሸለቆ እስከ ሜዲቴራኒያን ባሕር ይደርሳል፤ ይህም የደቡብ ድንበር ነው።

20 “የምዕራቡ ድንበር የሜድትራኒያን ባሕር ሆኖ፥ እስከ ሐማት መግቢያ አንጻር ድረስ ይደርሳል። ይህም የምዕራቡ ድንበር ይሆናል።

21 “ይህችን ምድር በእስራኤል ነገዶች መካከል ተከፋፈሉአት።

22 ዘላቂ ርስትም ትሁንላችሁ፤ ልጆች ወልደው በመካከላችሁ የሚኖሩ ባዕዳንም ምድሪቱን በምትካፈሉበት ጊዜ የራሳቸው ድርሻ ይኑራቸው፤ እንደማንኛውም እስራኤላውያን ዜጋ ተቈጥረው ምድሪቱን ከሚካፈሉት ከእስራኤል ነገዶች ጋር ዕጣ እንዲጣልላቸው ያስፈልጋል።

23 በእስራኤል የሚኖር እያንዳንዱ የውጪ አገር ተወላጅ አብሮ ከሚኖረው ከእስራኤል ሕዝብ ነገድ ጋር የራሱ ድርሻ ይኑረው፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告